ሚዲያና የኢትዮጵያ ምርጫ
የኢትዮጵያ ምርጫዎችን ውጤት በመወሰን ረገድ የሚዲያ ተቋማት ሚና ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ ወጥ ምላሽ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አብዛኛው ከሚዲያ ተቋማቱ ባለቤትነት ጋር ይያያዛል፡፡ የሰፊው ሕዝብ የመረጃ ምንጭ የሆነው የብሮድካስት ሚዲያ በተለይ በመንግሥት ቁጥር ሥር ያለና ሞኖፖሊ ሊባል በሚችል ደረጃ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል የሚያገለግል ተቋም እንዲሆን አድርጎታል በሚል የሚከራከሩ አካላት፣ የግል የኅትመት የሚዲያ ተቋማት በመረጃ ምንጭነት የሚያገለግሉት ጥቂት ሺሕ የከተማ ልሂቃንን ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሚዲያ ከባለቤትነት ተፅዕኖ ይልቅ በሙያው ተቀባይነት ባለው መርህ መሠረት ነፃና ገለልተኛ በመሆን አለማገልገሉን እንደ ትልቅ ስንክሳር የሚወስዱም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል የአገሪቱ የበላይ ሕግ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 29(5) ላይ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ተብሎ መደንገጉን ያስታውሳሉ፡፡ በተጨማሪም እንደ ሸገርና ዛሚ ያሉ የሬዲዮ ጣቢያዎች በመንግሥት ቁጥጥር ናቸው ሊባሉ እንደማይችሉ ይከራከራሉ፡፡ የግሉ የኅትመት ዘርፍም በመንግሥት ተፅዕኖ አይታማ እንጂ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች አካላት ተፅዕኖ ራሱን ያላፀዳ መሆኑ በእንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደፈጠረበት ያወሳሉ፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ የእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ‹‹ሚዲያና ምርጫ የኢትዮጵያ ልምድና ለ2007 ምርጫ ያሉት አንድምታዎች›› በሚል ርዕስ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት፣ ከዩኒቨርሲቲው የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ጋር ለ