በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በተከሰሱት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ምስክሮች መሰማት ጀመሩ
Reporter የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሽብርተኝነት ክስ በመሠረተባቸው ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ላይ ምስክሮቹን ከመጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ማሰማት ጀመረ፡፡ ዓቃቤ ሕግ መጋቢት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ባስያዘው ጭብጥ፣ በዕለቱ ያቀረባቸው ምስክሮች የደረጃ ወይም ታዛቢ ምስክሮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ የሚመሰክሩትም ፖሊስ በተከሳሾቹ ቤት፣ በቢሮአቸውና በማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ፣ ከተከሳሾቹ ላይ የተገኙ ማስረጃዎች የእነሱ መሆናቸውን አምነው ሲፈርሙ ማየታቸውንና እነሱም መፈረማቸውን መሆኑን ገልጿል፡፡ ታዛቢ ምስክሮቹ አንዳንዶቹ ለግል ጉዳያቸው በፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) ሄደው ፖሊስ ታዛቢ እንዲሆኑለት ሲጠይቃቸው፣ በፈቃደኝነት የታዘቡ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ ከራሳቸው ላፕቶፕ ላይ (አንዳንዶቹ) የአማርኛና እንግሊዝኛ ጽሑፎችን ማየታቸውንና ርዕስ ርዕሱን ማንበባቸውን ገልጸዋል፡፡ አቤል ዋበላ የተባለው ጦማሪ በራሱ የይለፍ ቃል (Pass Word) ላፕቶፑ ተከፍቶ የታተመ ‹‹አፍሪካን ሪቪው›› የሚል በእንግሊዝኛ የተጻፈ ነገር ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ ‹‹ወያኔ ወይኔ ጉዱ›› የሚል ርዕስ ያለው ጽሑፍ ደግሞ የበፈቃዱ ኃይሉ ላፕቶፕ ተከፍቶ ሲታተም ማየታቸውን መስክረዋል፡፡ አንድ ታዛቢ የታዘቡትና ምስክር የፈረሙት በጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ ላይ መሆኑን ቢገልጹም፣ አስማማውን ከስም በስተቀር በአካል መለየት አቅቷቸዋል፡፡ ቀረብ ብለው እንዲለዩት ቢደረግም ጦማሪ አቤል ዋበላን ‹‹እሱ ነው›› ብለው ደጋግመው ከመናገር ያለፈ አስማማውን መለየት ባለመቻላቸው የችሎት ታዳሚውን አስፈግገዋል፡፡ ሌሎቹም ምስክሮች ተመሳሳይ ምስክርነት በመስጠት ተከሳሾቹ ከፈረሙ በኋላ እነሱም በሰነዱ ላይ መፈ