‹‹ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች እንዲህ እናደርጋቸዋለን የሚሏቸው ነገሮች እጅግ ጠቅለል ያሉና ያልተጣሩ ናቸው›› ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ
ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ በርካታ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል ትልቅ ትኩረት የሰጡት በገዥውና በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባህርይ ላይ ነው፡፡ ይህን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ በሚያሳዩት ባህርይ ዙሪያ ሰለሞን ጎሹ ዶ/ር ካሣሁን ብርሃኑን አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የምርጫ ቅስቀሳ አስፈላጊነትን እንዴት ይገልጹታል? ዶ/ር ካሣሁን፡- ብዙ ፓርቲዎች በሕግ ተፈቅዶ በሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ አስፈላጊ ነው፡፡ ፓርቲዎች የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ፕሮግራም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ሥርዓቱ የምርጫ ውድድርን የሚፈቅድ መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም የምርጫ ቅስቀሳ እንደ ኢሕአፓና መኢሶን በድብቅ የምታካሂደው አይደለም፡፡ ሕዝቡን በግልጽ ሰብስበህ ፕሮግራምህን የምታስተዋውቅበትና ከሌሎች የሚሻልበትን መንገድ የምታሳይበት ዘዴ ነው፡፡ ፓርቲው ሥልጣን ቢይዝ ከሌሎች በተሻለ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት እንደሚያሟላ፣ የአገሪቱን ጥቅም እንደሚያስጠብቅ፣ የኅብረተሰቡን ደኅንነት እንደሚጠብቅ የሚገልጽበት መሣሪያ ነው፡፡ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን በየጊዜው ሊያስተዋውቁ ይችላሉ፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ ግን በምርጫ ጊዜ ነው የሚካሄደው፡፡ በተቻለ መጠን የምርጫ ድጋፍ የሚያሰባስቡበት ነው፡፡ የምርጫ ቅስቀሳን በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የገንዘብ አቅም፣ የሚዲያ ተደራሽነት፣ አመቺ ደኅንነትና ነፃነት ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ ለጤናማ የብዙኃን ፓርቲ ውድድር አመቺ ነው ወይ የሚለው በእርግጥ አጠያያቂ ነው፡፡ ለምሳሌ የሕዝብ ወይም የመንግሥት ሚዲያን በእኩልነት ባይሆን እንኳን