በሐዋሳ የሚቋቋመው ኢንዱስትሪ ዞን የውጭ ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል
የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ኢንዱስትሪ ዞን የበርካታ ኩባንያዎችን ትኩረት በመሳቡ፣ በዚህ የኢንዱስትሪ ዞን ኢንቨስት ለማድረግ የቻይና፣ የህንድና የሲሪላንካ ኩባንያዎች ቦታ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት ዋና አማካሪና ልዩ ረዳት አቶ አኒሳ መልኮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእነዚህ ኩባንያዎች ጥያቄ እየታየ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት በቅርብ አራት ከተሞችን የኢንዱስትሪ ቀጣናዎች አድርጎ መርጧል፡፡ እነዚህ ከተሞች አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻና ሐዋሳ ናቸው፡፡ በሐዋሳ አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሁሉም ነገር የተሟላለት የኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከአዲስ አበባ በ275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሐዋሳ ከተማ በቅርቡ የአውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባ በመወሰኑ፣ በርካታ ኢንቨስተሮች ትኩረት እንዲያደርጉ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አቶ አኒሳ እንዳሉት ከአውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስከ ሐዋሳ ከተማ ድረስ፣ እንዲሁም ከሐዋሳ አልፎ እስከ ኬንያ ድረስ የባቡር መስመር ይዘረጋል፡፡ የባቡር መስመር የሚዘረጋ ከሆነ በርካታ ኩባንያዎች በሐዋሳ ኢንቨስት ለማድረግ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እንደገለጹም ታውቋል፡፡ በሐዋሳ የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን በተለይ አግሮ ፕሮሰሲንግ ላይ እንደሚያተኩር አቶ አኒሳ ገልጸው፣ አካባቢው የግብርና ምርቶች በሰፊው የሚገኙበት በመሆኑ የኢንዱስትሪ ዞኑ ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ቀደም ብሎ ለኢንዱስትሪ የተከለለው ቦታ ላይ ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ፣ ጋትስ አግሮ ኢንዱስትሪና የመሳሰሉት ኩባንያዎች ምግብና መጠጦችን በማምረት ላይ