የተጨማሪ እሴትና የገቢ ግብር ሕጐች እንዲሻሻሉ ጥያቄ ቀረበ
የተጨማሪ እሴትና የገቢ ግብር ሕጐች ጥናትን መሠረት ያደረገ ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ከአሥር ዓመታት በላይ ሥራ ላይ መዋላቸው፣ የታክስ መርህን የሚፃረር መሆኑ በጥናት ተመለከተ፡፡ ፎረም ፎር ሶቫል ስተዲስ (FSS) ጥር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ ላይ ‹‹የታክስ ሕጐችና ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና የአካውንቲንግ ትምህርት ክፍል መምህር ዶ/ር ወለላ አቤሆዴ እንዳብራሩት፣ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ለውጦች የተስተዋሉ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2002 ሥራ ላይ የዋሉት እነዚህ የግብር ዓይነቶች ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳይደረግባቸው ለአሥራ ሦስት ዓመት መዝለቃቸው ችግር ነው፡፡ ‹‹ታክስ በባህሪው ለውጦች ከሥር ከሥር እየታዩ ሁኔታዎች እንዲጣጣሙ የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሕጐቹ ብዙ ለውጥ ሳይደረግባቸው በሥራ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል የጥናቱ አቅራቢ፡፡ በእነዚህ የታክስ ሕጐች ላይ ለውጥ ሳይደረግ እስካሁን ሥራ ላይ መዋላቸው የፈጠረውን ተፅዕኖ የሚያመለክተው ጥናቱ፣ የገቢ ግብር ሕግን በመጥቀስ በሕጉ መሠረት የሠራተኛ ደመወዝ የመጀመሪያው 150 ብር ከታክስ ነፃ ቢሆንም በዛሬ ግሽበት የዚህ ገንዘብ መጠን ከግብር ነፃ መሆን ትርጉም የሚሰጥ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ከድህነት ወለል አንፃር ቢታይም ትርጉም የሌለው መሆኑን፣ የቢዝነሶች ከግብር ነፃ የሚሆንበት የመጀመሪያው 1,800 ብርም በተመሳሳይ ትርጉም አልባ አሠራር መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ የገቢ ግብር የምጣኔ ወሰኖች ቢታዩ፣ ከፍተኛው የገቢ ግብር መጣል የሚጀምርበት 5,000 ብር አቅሙ የተሸረሸረ በመሆኑ የታክስ መጠኑን ማሻሻል የግድ እንደሆነ ጥናት አቅራቢዋ ገልጸዋል፡፡ የድርጅቶች ደረጃ