የተጫዋቾች የዝውውር ረቂቅ ሰነድ ለምን አነጋጋሪ ሆነ?
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከስድስት አሠርታት በላይ እንዳስቆጠረ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ታሪካዊ ጉዞው ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች ከመነሻው እንደሌሎቹ አገሮች ወጥ የሆነ አደረጃጀት ኖሯቸው ሊቀጥሉ ባለመቻላቸው ዛሬም በተለያዩ የአሠራር ክፍተቶች እሰጣ ገባ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣ የአገሪቱ ክለቦች በፊፋ የክለብ አደረጃጀትና የተጨዋቾች የዝውውር መርሕ እንዲተዳደሩ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱ እንደማሳያ ሊወሰድ እንደሚገባውም የሚናገሩ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ክለቦች በአገሪቱ የሚፈፀመው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ በፊፋ ዝቅተኛውን የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር መስፈርት ያሟላ እንዲሆን፣ በተጨማሪም አሠራሩ በሕጋዊ ወኪል እንዲመራና ሒደቱም ተጨዋቾችን፣ ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ በማድረግ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ዕድገት መፋጠን የራሱን አወንታዊ ሚና ይጫወታል በሚል የተለያዩ አንቀፆችን የያዘ የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ረቂቅ ሰነዱ ከጥር 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በኋላ ሕጋዊ መመሪያ ሆኖ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እንደሚፀድቅና እስከዚያ ግን ክለቦች በረቂቅ ሰነዱ በተካተቱ ነጥቦች ውስጥ አለን የሚሉትን ሐሳብ እንዲያንሸራሽሩ ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ፌዴሬሽኑና ክለቦች በካፒታል ሆቴል ባደረጉት የመጀመሪያ የውይይት መድረክ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ሆኖም ግን መመሪያው ደንብ ሆኖ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ረቂቅ ሰነዱ ለክለቦች ቀደም ብሎ እንዲደርስ ተደርጎ በተለይ የክለብ አስተዳዳሪዎችና ባለቤቶች ጉዳዩን በሰከነና በጥልቀት እንዲመክሩበት መደረግ ነበረበት በሚል አንዳ