ሲኣንን በኣባልነት የያዘው መድረክ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ፣ በሕጉ መሠረት የተከናወነ ባለመሆኑ እንዲደገም ጥያቄ አቀረበ፡፡ መድረክ ይኼን ያስታወቀው ባለፈው ዓርብ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤቱ ነው፡፡ ‹‹ያለ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚና የሕዝብ ታዛቢ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ምርጫ ሊኖር ስለማይችል፣ ኢሕአዴግ ከሀቀኛ ታቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ ይደራደር፤›› በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫውን የሰጡት የመድረክ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ዶ/ር መረራ ጉዲናና ዋና ጸሐፊው አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም ሲሆኑ፣ ከምርጫው ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን አንስተው ገለጻ አድርገዋል፡፡ ‹‹ታኅሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በሕጉ መሠረት የተከናወነ ባለመሆኑ፣ የምርጫውን ሕግጋት ባከበረ መንገድ በድጋሚ እንዲካሄድ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያካሄደውን የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሠረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደብዳቤ ተጠርተው በተገኙበት ሳይሆን፣ የኢሕአዴግ አባላት የተሰየሙበት በመሆኑ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በአዋጁ አንቀጽ 82 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 መሠረት ለሕዝቡና ሕጋዊ ዕውቅና ላላቸው ፓርቲዎች ጥሪ ተደርጎ ገለልተኝነታቸው እየተረጋገጠ እንዲመረጡ እንጠይቃለን፤›› በማለት አዲስ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡ መግለጫው በዋንኛነት ያተኮረው በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት የተመለከቱና ሌሎች ተያያዥ ጉ