በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ፒቪኤች ግሩፕ በሐዋሳ ከተማ የራሱን ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ተሰማ
በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ ፒቪኤች ግሩፕ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለመክፈትና ሩቅ ምሥራቅ የሚገኙ ደንበኞቹም ፋብሪካዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዛውሩ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር እየተደራደረ መሆኑን ምንጮች ገለጹ፡፡ ቶሚ ሂልፊገር፣ ካልቪን ክሊን፣ ቲምበርላንድና አይዞድ በሚባሉ የልብስ ብራንዶች የሚታወቀው ይህ ግዙፍ ኩባንያ፣ የደቡብ ክልል መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ የራሱን ፋብሪካ የማቋቋም ዕቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡ ኩባንያው ራሱ ከሚያቋቁመው ፋብሪካ በተጨማሪ፣ ሩቅ ምሥራቅ በሚገኙ አገሮች ልብስ አምራች ደንበኞቹ ፋብሪካቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዛውሩ ፍላጎት አሳይቷል፡፡ የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር እየመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ በመምጣት ድሬዳዋ፣ ሐዋሳና አዲስ አበባ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ዞኖችን ጎብኝተዋል፡፡ በቆይታቸው ወቅት የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ከመጎብኘታቸውም በተጨማሪ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ጋር በወደፊት ዕቅዶች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ፒቪኤች ግሩፕ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ የአልባሳት ገዥና ሻጭ ነው፡፡ ኩባንያው ለደንበኞቹ የገንዘብ አቅርቦት ያመቻቻል፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማርኬቲንግ ኃላፊ አቶ ያሬድ መስፍን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው 60 ሺሕ ሔክታር መሬት ለጥጥ ልማት ጠይቋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በጥጥ ልማት የሚሆን መሬት በደቡብ ክልል በማፈላለግ ላይ ነው ብለዋል፡፡ እ.ኤ.አ.