ዋሊያዎቹ ቅዳሜ ማሊን ያስተናግዳሉ
ብዙ ድካምና ጉልበት ብቻ ሳይሆን፣ ከውጤቱ አንፃር ብዙ ገንዘብም እየፈሰሰበት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚፈለገውን ነጥብ ማስገኘት ሳይችል ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ የምድቡን ሦስተኛ ጨዋታ ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም የማሊ አቻውን ያስተናግዳል፡፡ የማሊ ቡድን ከነገ በስቲያ ዓርብ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በሜዳቸው በአልጄሪያ፣ ከሜዳቸው ውጪ ደግሞ በማላዊ ሁለት ሽንፈቶችን ያስተናገዱት የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ፣ ለቅዳሜው ጨዋታ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ 27 ተጨዋቾችን ይዘው በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ የሚቀንሷቸውን ተጨዋቾች አስመልክቶ አሠልጣኙም ሆነ ፌዴሬሽኑ ምንም ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ግን ደግሞ የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ከአምስት ቀን በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 5 ቀን ስለሚሆን በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ አሠልጣኙ የመጨረሻዎቹን ተጨዋቾች ለፌዴሬሽኑ እንዲያሳውቁ በፌዴሬሽኑ በኩል ጥያቄ መቅረቡ እንደማይቀር የሚገልጹ አሉ፡፡ አሠልጣኝ ማሪያኖ ቀደም ሲል ከመረጧቸው ተጨዋቾ በተጨማሪ በግብፅ የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለና ኡመድ ኡክሪ፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ፣ በአውሮፓ ከሚጫወቱት ደግሞ የሱፍ ሳላህ፣ አሚን አስካርና ዋሊድ አታ ዋሊያዎቹን የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ከአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናው ዴቪድ በሻህና የደደቢቱ ሔኖክ ካሳሁን በተመሳሳይ በአዲስ መልክ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽን ምንጮች አሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶና የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ በቡድኑ ውጤት ዙሪያ መግባባት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ አሠልጣኙ በበኩላቸው፣ ከደጋፊው