በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥልጠና ሥጋት የሆነው ርዕዮተ ዓለማዊ ጫና
አንዳንድ የታሪክ ሰነዶችና መጻሕፍት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ‘ተማሪ-መራሽ’ ፖለቲካ ይሉታል፡፡ የተደራጀ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የፈለቀው በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆን፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታትን ከሥልጣን ለማፈናቀል የተማሪዎች ሚና ቁልፍ ነበር፡፡ የወቅቱ የኢሕአዴግ መሪዎች የፖለቲካና የትጥቅ ትግል ለማድረግ የወሰኑት፣ ህልምና ራዕያቸውን የነደፉት በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ያኔ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ይጠራ በነበረው) ነበር፡፡ እነዚህ የኢሕአዴግ መሪዎች ካሳኳቸው ድሎች አንዱ የሆነው የየካቲት 1966 አብዮት 40ኛ ዓመት ከተዘከረ ከጥቂት ወራት በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በመላው አገሪቱ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የመንግሥትን ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ባለመ ሥልጠና ላይ እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ ከ40 ዓመት በፊት የተለያዩ አመለካከቶችን ለመጨፍለቅ ሞክሯል ባሉት መንግሥት ላይ ያመፁት ወጣቶች ያመጡት አብዮት በደርግ ተዘርፏል በማለት የትጥቅ ትግል አድርገው ሁለተኛ ለውጥ ቢጎናፀፉም፣ ይህ ሥልጠና በቀድሞዎቹ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአሁኑ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች የበላይነት ሲካሄድ ከገዥው ፓርቲ አመለካከት ውጪ ያሉ አማራጭ ሐሳቦችን ይጨፈልቃሉ መባሉ የታሪክ ምፀት ሆኗል፡፡ በመልካም አስተዳደር፣ በዲሞክራሲ ግንባታና በልማት ሥራዎች ላይ ያተኩራል በተባለው ሥልጠና፣ የሥልጠናው አስገዳጅነትና በይዘቱ ርዕዮተ ዓለማዊ አዝማሚያ ላይ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በሥልጠናው ጊዜ፣ ወጪና በኢሕአዴግና በትምህርት ሚኒስቴር ሚናዎች ላይም አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በመንግሥት መካከል ስላለው ልዩነት፣ በመንግሥትና በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ስላለው ግንኙነትና የዩኒቨርሲቲዎች