ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን እየሆኑ ነው?
ምርጫ 2007 ዘጠኝ ወራት ያህል እየቀሩት ነው፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን የሚያዘጋጁበት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር የቤት ሥራቸውን የሚያጠናቅቁበትና ምርጫው ምርጫ እንዲመስል የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡበት ነው፡፡ አሁን እያየን ያለነው ግን ይህንን ምሥል ሳይሆን ተቃራኒውን ነው፡፡ የምርጫ ሸብ ረብ ሳይሆን በትንሽ በትልቁ እርስ በርስ መናቆር ነው፡፡ በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ አለን የሚሉት ስማቸው ጎላ ብሎ የሚታይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሽኩቻ ውስጥ ናቸው፡፡ ከገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር ለዓመታት የከረሙበት መናቆር እንዳለ ሆኖ፣ አሁን ደግሞ ወደ ውስጥ ግብግብ ገብተዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መጠናከር ሳይሆን መፍረክረክ እየታየ ነው፡፡ ምርጫ ዋዜማ ላይ ሆኖ ይህንን ትርምስ የሚታዘቡ ደጋፊዎችም ሆኑ አባላት ተስፋ እየቆረጡ ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ትግሉንም ሊሸሹ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አይበጅም፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚደረግ ሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና አስፈላጊ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የሚያብበው መራጩ ሕዝብ የተለያዩ አማራጮች ያሉዋቸውን ፓርቲዎች ማግኘት ሲችል ነው፡፡ አማራጭ ሲባል ለይስሙላ የሚነገር በጥናት ላይ ያልተመሠረተ ስንክሳር ሳይሆን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተደራጁ ፕሮግራሞችን ይዞ መቅረብ ነው፡፡ አሁን የምናየው ይህንን አይገልጽም፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ለእንቅስቃሴዎቻቸው መገደብ ሁለት ዓበይት ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ውጪያዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ውስጣዊ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ውጫዊው ምክንያት በገዥው ፓርቲ ተፅዕኖ የሚገለጽ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ምኅዳሩን ከማጥበብ አንስቶ በርካታ ምክንያቶች የሚቀርቡበት ተፅዕኖ ብዙ የተባለበት በመሆ