በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚስፋፋው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ
ፎቶ ከ ሪፖርተር ጋዜጣ ሐዋሳ ከተማ እንደ ዕድሜ ለጋነቷ ሁሉ በውስጧ አቅፋ የያዘቻቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ዕድሜ ከሁለት አሠርት ብዙም አይርቅም፡፡ ወንዶ ገነት ደንና ተፈጥሮ ኮሌጅን፣ ሐዋሳ ግብርና ኮሌጅን፣ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅንና ሌሎችን ጨምሮ የያዘው ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ ሲያስመርቅ የዘንድሮው ለ15ኛ ጊዜ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ከሁሉም ተቋማቱ 4,276 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት በቅድመ ምረቃ የነበሩት ስምንት የሥልጠና መስኮች ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት መስኩን ወደ 67 አሳድጎ በድኅረ ምረቃ 52 ፕሮግራሞችን ከፍቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሰባቱ የዶክትሬት (ፒኤችዲ) ዲግሪ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ከመማር ማስተማሩ ሒደትና ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ደረጀ ጠገናው የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሴፍ ማሞን አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት መሠረታዊ ዓላማና ከዕድሜው ለጋነት አኳያ ምን ያህል ኃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ይቻላል? ዶ/ር ዮሴፍ፡- ዩኒቨርሲቲው አምስት ካምፓሶች ያሉት ሲሆን፣ በሰባት ኮሌጆችና በአንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተደራጀ ነው፡፡ ከሐዋሳ ዋናው ግቢ፣ ግብርና ኮሌጅ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች በተጨማሪ፣ በይርጋለም የሚገኘው የሐዋሳ ካምፓስና ወንዶገነት ደንና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች የዩኒቨርሲቲው አካል ናቸው፡፡ በዚህ መነሻነት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት መሠረታዊ መርሆዎች ማለትም መማር ማስተማር፣ ምርምር፣ የኅብረተሰብ አገልግሎትና የቴከኖሎጂ ሽግግር አኳያ በ2006 የትምህርት ዘመን ከመንግሥት በተመደበለት 1.2 ቢሊዮን ብር በጀት መጠነ ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል፡