ደመወዛችን ሃምሳ ጉዳያችን መቶ!
እነሆ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ልንጓዝ ነው። አጀማመራችን በፀጥታ የተጠነሰሰ ነው። የዛሬዎቹ ተሳፋሪዎች ትንፋሽ ያላቸው አይመስሉም። በውጥረት የታፈነው ጎዳና መንገደኛውን መተንፈሻ የነሳው ይመስላል። ጩኸት ኑሮው የሆነው ወያላ ዕድሜው በለቅሶ ተጀምሮ በጩኸት በሚገባደድ ሕዝብ መሀል ያለ ዕረፍት ይጣራል። እንደ ንጋት ጎርናና ድምፁ ሁሉ ጎርበጥባጣ ኑሮው ይለሰልስለት ይመስል እሪ ሲል አይታክትም። ጥሪ በማይፈልገው የትግል ጎዳናችን ላይ ግን የወያላው ልፋት መና የቀረ ይመስላል። ከወዲያ ወዲህ ሲሯሯጥ ከቆየ በኋላ አካባቢውን የሚቀያይረው ሕዝብ ፍልሰቱ መቼም የሚቆም አይመስልም። ሰው የሚደርስበትን ቦታ እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለሥራው እያውጠነጠነ ባላሰበው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የህልማችንና የሩጫችን ውጤት በአብዛኛው አንገት ያስደፋል። ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። ማጠቃለያ ሐሳብ ይሰጠው ሲባል ግን ቃሏ አንዲት ናት። እሷም ‘ተግዳሮት’ ትባላለች። መውጣትና መውረድ አክርማና ስንደዶ ሆነው ያልቀየሱት ጎዳና በእርግጥ በየትም አገር ታሪክ አይኖርም። ነፃ ብሎ መንገድ፣ እንደ ጨርቅ የሚጠቀለል አልጋ ባልጋ ጎዳና ለሰው ልጅ አይገባውም የተባለ የተፈጥሮ ሕግ ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ተግዳሮቱና ሸሩ በማያልቅ የሰው ልጅ ሕይወት ሁሉም እንደራሱ አረማመድ እየተጓዘ እንደ ሕዝብ ደግሞ በጋራ መጓጓዣ እንዝርቱ ይፈትላል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክና ለታዛቢ በሩን ይከፍታል። መንገድ ሁሉን ይዳኛል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን እያደር በርትቷል። መቼም