የኮሪያ መንግሥት ለሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ የፈቀደው ብድር ለፓርላማ ቀረበ
ከሞጆ-ሐዋሳ የመጀመሪያ ዙር የፍጥነት መንገድ ግንባታ የኮሪያ መንግሥት ኤግዚም ባንክ የፈቀደው 100 ሚሊዮን ዶላር ብድር ለፓርላማ ቀረበ፡፡ የሞጆ-ሐዋሳ መንገድ 201 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ ግንባታው በሁለት ዙር ተከፍሎ የሚገነባ ነው፡፡ የጀመሪያው ዙር ግንባታ ከሞጆ-ዝዋይ በራሱ በሁለት ተከፍሎ የሚገነባ መሆኑን የብድር ማፅደቂያ አዋጁ አባሪ ሰነድ ያብራራል፡፡ የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ከሞጆ-መቂ ሲሆን፣ ለዚህ ግንባታ ማስፈጸሚያ የሚውል 128 ሚሊዮን 460 ሺሕ ዶላር በዚህ ዓመት ከአፍሪካ ልማት ባንክ መገኘቱን ሰነዱ ያብራራል፡፡ ለቀሪው የመቂ-ዝዋይ መንገድ ግንባታ ደግሞ የኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት (ኤግዚም) ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላር መፈረሙን የአዋጁ አባሪ ይገልጻል፡፡ ከሞጆ-ሐዋሳ ድረስ የሚገነባው የፍጥነት መንገድ በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን እንዲያስተናግድ ይፈለጋል፡፡ አጠቃላይ ወጪውም 349 ሚሊዮን 480 ሺሕ ዶላር መሆኑን ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ከኮሪያ መንግሥት የተገኘው 100 ሚሊዮን ዶላር የ15 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ ትግበራ ባንኩ በሚፈጽመው ክፍያ ላይ 0.1 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ከብድሩ ገንዘብ ላይ ተቀንሶ እንደሚከፈል፣ ጥቅም ላይ ባልዋለውና ባልተከፈለው የብድር ገንዘብ ላይ ደግሞ 0.01 በመቶ ወለድ እንደሚታሰብበት ረቂቅ ማፅደቂያ አዋጁ ይገልጻል፡፡ የብድር ስምምነቱ እስከዛሬ ከነበሩት የብድር ዓይነቶች ጋር ሲነፃፀር የ55 ዓመት መሆኑ፣ የአገልግሎት ክፍያውና ወለዱ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ የፓርላማው አባላትን አስደንቋል፡፡ ‹‹የኮሪያ ኤግዚም ባንክ ብድር ሳይሆን ስጦታ ነው የሰጠው፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ ዶ/ር አድሃና ኃይሌ አድንቀውታ