መድረክ ፓርቲ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ
ምንጭ፦ ሬዲዮ ፋና አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 16 ፣ 2006 ( ኤፍ.ቢ.ሲ. ) የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ፓርቲ ዛሬ በአዲስ አበባ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ። የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች መነሻቸውን ግንፍሌ ወንዝ ድልድይ ቅዱስ ማቲዎስ አንግሊካን ቤተክርስቲያን አድርገው ፥ በህንድ ኤምባሲ በመታጠፍ አቧሬ አደባባይን ፣ አድዋ ድልድይን በማቋረጥ ማጠቃለያቸውን የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 በተለምዶ ታቦት ማደሪያ እየተባለ በሚጠራው ሜዳ ላይ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ ኢህአዴግ ለሰላማዊ ድርድር በሩን ክፍት ያድርግ ፤ በአንድነት ኢትዮጵያን እንገነባለን ፤ የፕሬስ ነፃነት ይከበር ፤ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ይፈቱ ፤ መልካም አስተዳደር እውን ይሁን እና የውሃ ፣ መብራትና ስልክ አገልግሎቶች ይስተካከሉ የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል። በሰልፉ ማጠቃለያ ላይ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ እና ዋና ፀሃፊው አቶ ገብሩ ገብረማሪያም ንግግር ያደረጉ ሲሆን ፥ ፓርቲው ባዘጋጃቸው ወቅታዊ ጥያቄዎች ላይ ኢህአዴግ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ የተዘጋጀው የጋራ ማስተር ፕላን ህዝባዊ ውይይት ተደርጎበት በህዝቡ መልካም ፈቃድ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባልም ብለዋል።