የኢኮኖሚ ዕድገቱ በብዙኃን ኢትዮጵያዊያን የኑሮ ጫና ሲመዘን
በአሳምነው ጎርፉ ያሳለፍናቸው ቀናት ኢትዮጵያዊያን የክርስትና እምነት ተከታዮች ዓብይ ፆምን ተሻግረው የፋሲካ በዓልን በድምቀት ያከበሩበት ነው፡፡ በዓል ሲመጣ ደግሞ ሐበሻ ‹‹እንደ ቤቴ›› ሳይሆን ‹‹እንደ ጎረቤቴ›› በሚል ብሂል አቅሙን አሟጦና ተበድሮ ለማድመቅና ‹ለመደሰት› እንደሚዳክር ይታወቃል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንደተዘገበውና በየአካባቢው ተዟዙሬ እንደተመለከትኩት ዘንድሮ የቁም እንስሳት፣ የቤት ዕቃውና ማስዋቢያው ብቻ ሳይሆን ከስኒ ረከቦት ሥር የሚጎዘጎዘው ቄጠማ ሳይቀር በፍጥነት ዋጋቸው አሻቅቦ ታይቷል፡፡ ተርፎት በቅንጦት ለሚኖረው ምንም ባይመስለውም፣ ብዙኃኑ ሕዝብና መካከለኛ ላይ ያለው ወገን የመግዛት አቅም አጥቶ ሲንፈራገጥ ታይቷል፡፡ በተለይ የደመወዝተኛው ችግር ደግሞ ይጎላል፡፡ እንግዲህ ይኼ ጉዳይ ነው በዚህ ርዕስ ላይ አንዳች ነገር ማለት እንደሚገባ ያነሳሳኝ፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ የገቢ መመጣጠን አሳይቷልን? በዚህ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት መኖሩን የሚክድ ካለ ጤነኝነቱ ያጠራጥራል፡፡ ስለዚህ ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ተከታዮች ‹‹ኒዮ ሊብራል›› የሚባለውን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ (የገበያ አክራሪነትም ይባላል) የሚተቹበት አንድ አባባል አለ፡፡ ‹‹የገቢ አለመመጣጠን በአብዛኛው የሚስተዋለው ባለሀብቶች ፖለቲካውን በጨበጡባቸው አገሮች ነው፡፡ ባለፀጋ ፖለቲከኞች ለመሠረታዊ የኅብረተሰብ አገልግሎቶች ማለትም ለትምህርት፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ለሕዝብ ትራንስፖርትና ለመሳሰሉት በቂ በጀት ለመመደብ ፈቃደኛ ስለማይሆኑ የታክስ ምጣኔውን በመቀነስ ጫናቸውን ከላያቸው ላይ ያራግፋሉ፤›› የሚል ነው፡፡ ይህን የሚቃወሙት የፖለቲካ ተንታኞች ግን የመንግሥትን በመሠረታዊ ልማቶች ላይ መሳተፍ አጥብቀው ባይቃወሙትም (