ከበጀት አጠቃቀም ግድፈት በተጨማሪ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣትም መላ ይፈለግለት
ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርት፣ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የበጀት አጠቃቀም ግድፈትና ብክነት መኖሩን አስታውቋል፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የሚታይ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን በመጠቆም ፓርላማው አፋጣኝ የሆነ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ በመንግሥት በጀት የሚያዝላቸው ብዙዎቹ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በዕቃ ግዥዎችና በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ደንብና መመርያ እንደሚጥሱ ስም ዝርዝራቸው ተጠቅሶ ተገልጿል፡፡ የአገር ሀብትን ከጥፋት ለመታደግ ሲባልም በአስቸኳይ ዕርምጃ ይወሰድ ዘንድ ለፓርላማው ጥሪ ቀርቧል፡፡ ይህ በባለሙያዎች ከፍተኛ ጥንቃቄና ሙያዊ ትንተና የቀረበ ሪፖርት በፓርላማውም ሆነ መንግሥትን በሚመራው አስፈጻሚ አካል ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው ጥርጥር የለውም፡፡ ከበጀት አጠቃቀም ግድፈትና ከብልሹ አሠራር በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ ተንሠራፍቶ ያለው ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት ችግር ነው፡፡ ከብቃት ማነስ በተጨማሪ ግድ የለሽነትና የአገልጋይነት መንፈስ መጥፋት በየቦታው ተንሠራፍቷል፡፡ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የሥነ ምግባር መርሆዎች በሚያማምሩ ኅብረ ቀለማት በተዋቡ ሰሌዳዎች ላይ በግልጽ ቦታ ላይ ተጽፈው ቢታዩም፣ እነዚህን መርሆዎች የሚቀናቀኑ በርካታ እኩይ ተግባራት ይፈጸማሉ፡፡ የመንግሥት ፖሊሲዎችን በአግባቡ እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው የተወሰኑ ወገኖች ለዜጎች ቅሬታና ምሬት ምክንያት እየሆኑ ናቸው፡፡ አገልግሎት ፈላጊዎች ወደተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ሲመጡ ግብር ከፋይ ዜጎች መሆናቸው፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸውና ጥያቄዎቻቸውም በአግባቡ መስተናገድ እንዳለበት ሊታወቅ ሲገባ እንግልት ነው የሚጠብቃቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በብዙዎ