ስለከሸፈው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ጥራዝ አንዳንድ ነጥቦች
በተስፋዬ ንዋይ መነሻ የአገራችንን የአጭር ጊዜ ታሪክ በጥልቀት ለሚመለከት ታዛቢ እጅግ በጣም የሚያሰቅቅና አፍ የሚያሲዘን ጉዳይ የተወሰኑ የዕውቀት ገመዶች የጥፋት ብርሃን ማስተላለፊያ በመሆናቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ በተጨባጭ እውነት ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊ ትንታኔ በበቂ ሁኔታ የተሰጠ አይመስለኝም፡፡ ይህ መሠረታዊ ሀቅ ንቅንቅ ወደማይል አለትነት የደረሰ ይመስላል፡፡ ይህን ችግር ከመሠረቱ የሚፈጥረው ደግሞ “የኢትዮጵያ ታሪክ” ተብሎ በጽሑፍም ሆነ በቃል የሚተረተረው ሐሳብ እውነታን መሠረት ያላደረገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለፖለቲካ፣ ግብዓትና ዓላማ ተብሎ የቀረበ ወይም እየቀረበ ያለ መሆኑ ነው፡፡ ይህ መምታታት አገሪቷን አንድ አስማሚ የሆነ ታሪክ የሌላት የሚያስመስላት ብቻ ሳይሆን የግልን የፖለቲካ ዓላማ ማካሄጃ መድረክ እንዲሆን ዕድል ፈጥሯል፡፡ የአገራችን የታሪክ ሒደትና ውጤት ላይ በእውነት (Authentic) ላይ የተመሠረተ የታሪክ ዕድገት በአገሪቷ ተመዝግቦ ያለመኖሩ አንድ ችግር ሆኖ፣ እነዚህ በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ታሪኮችን ከእውነት በላይ አድርጎ በመውሰድ ምሁራዊ ትንታኔዎችን በእነሱ ላይ መስጠት ሌላው አበሳጭ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን እንድል ያደረገኝ በቅርቡ በገበያ ላይ ውሎ የተሰራጨውን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ጥራዝ አንብቤ ከጨረስኩኝ በኋላ ነው፡፡ ይህ ጥራዝ የተጻፈው መስፍን ወልደማርያም በሚባሉ ግለሰብ (እኚህ ግለሰብ ፕሮፌሰር የሚል ማዕረግ የደረቡ ቢሆንም በመጽሐፉ ላይ ስላወለቁት እኔም ትቼዋለሁ) ሲሆን፣ በዚህ አጭር በማይባል ጥራዝ ጸሐፊው ያሉዋቸውን አስተሳሰቦችና ከአስተሳሰቦቹ ጀርባ ያሉትን መነሻዎች በሚገባን ቋንቋ አቅርበዋል፡፡ በዚህ ጥራዝ የታጨቁት ሐሳቦች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም፣ በዚህች አ