የተንከባለሉ የማንነት ጥያቄዎች
ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የፀደቀው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ዛሬ ሥራ ላይ ከዋለ 19ኛ ዓመቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥሙም በአገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመምራት የሚያስችል ሰነድ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎች ሕገ መንግሥቶች በሕዝቦች መካከል የተገባ ቃል ኪዳን አይደለም፡፡ ይልቁንም በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የተገባ ቃል ኪዳን ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት ለተሰጣቸው ለእነዚህ ቡድኖች ሕገ መንግሥቱ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፡፡ ከአንድነት ባልተናነሰ ሁኔታ ልዩነትና የማንነት ጥያቄ በሕግም ሆነ በተግባር ድጋፍ እንደሚሰጠው ይገመታል፡፡ የሕገ መንግሥቱን የተለያዩ አንቀጾች በማየት የማንነት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አላቸው ከማለትም በላይ እነዚህ አንቀጾችና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መርህን በማንገብ ታግሎና አታግሎ በአሸናፊነት ሥልጣን የያዘው፣ በሕገ መንግሥት ማርቀቅ ሒደቱም ወሳኝ ሚና ያለው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለተግባራዊነቱ ታማኝና ቁርጠኛ ነው የሚል ግምትም በብዙዎች ዘንድ ሥር የሰደደ ነበር፡፡ ይሁንና በተግባር ኢሕአዴግ የመገንጠልን፣ ክልል የመሆንና የማንነት ጥያቄዎችን በተለያዩ ጊዜያት ላነሱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሰጠው ምላሽ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሕገ መንግሥቱ ዋነኛ መሠረት የሆነው መርህ በሥራ ላይ ያለውን የመንግሥት ቅርፅ እንዲለውጥ በሚያስችል ሁኔታ እንዲተገበር ፍላጎት እንደሌለው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በቅርቡ ለህትመት የበቃው ‹‹የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄና የማዕከላዊ መንግሥታት ምላሽ ከአፄ ዮሐንስ