የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቁንጥጫ በርትቷል
ፎቶ ሪፖርተር ጋዜጣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ግቦች መሠረት በማድረግ የተጀመሩ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ፈርጀ ብዙ ግንባታዎች በሚካሄዱበት አገር ውስጥ ለዓመታት አስቸጋሪ የነበሩ ኋላ ቀር የአገልግሎት ዘርፎች የሚፈጥሩትን ችግር እያየን ነው፡፡ ከኋላ ቀር አሠራርና አኗኗር ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት መሰናክል ሲሆኑበትም ይታያል፡፡ እነዚህን መሰናክሎች እንዲህ ማየት የግድ ይላል፡፡ 1.የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ምንም እንኳን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ማጠቃለያ ላይ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አቅም አሥር ሺሕ ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል ቢባልም፣ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎች የሚገኘውን ከሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል በቅጡ ማሰራጨት አልተቻለም፡፡ ለትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሳካት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ትላልቅና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በኃይል መቆራረጥና እጥረት ምክንያት ማምረት እየተቸገሩ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ኢቨስትመንት የፈሰሰባቸው የተለያዩ የንግድ፣ የማምረቻና የአገልግሎት ተቋማት በኃይል መቋረጥ ምክንያት ለኪሳራ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ የባንክ ብድር መመለስ እስኪያቅታቸው ድረስ ምርት እየተስተጓጐለባቸው ነው፡፡ የተመረተውን ምርት መሸጥ አልተቻለም፡፡ ሆቴሎች ለጄኔሬተርና መሰል የኃይል አማራጮች ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረጉ ናቸው፡፡ በኢንቨስትመንት አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት እያጋጠመ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በቢሮዎች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በመሳሰሉት ከግለሰብ እስከ አገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ ሕፃናትን መመገብና መንከባከብ የማይቻልበት ደረጃ እየተደረሰ ነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃ እንኳ ቢታይ