የቡና ዘርፍን በባለቤትነት የሚያስተዳድር ድርጅት ሊቋቋም ነው
ባለቤት የሌለውን የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ባለቤት እንዲኖረው ለማድረግ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሚገኙበት ልዑካን ቡድን የሌሎች አገሮች ልምድ በመቅሰም ሥራ ላይ ተጠምዷል፡፡ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ቡናን በበላይነት የሚመራ መንግሥታዊ ተቋም ይቋቋማል ተብሏል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ የሚመራ ልዑካን ቡድን ብራዚልና ኮሎምቢያ በመጓዝ፣ አገሮቹ የቡናን ዘርፍ እንዴት እንደሚመሩ ልምድ ቀስሞ ተመልሷል፡፡ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ያዕቆብ ያላ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የፖሊሲና የዕቅድ አፈጻጸም ቁጥጥር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ያሉበት የልዑካን ቡድን ጓቴማላና ኮስታሪካ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ ለመቅሰም ተጉዟል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የቡና ዘርፍ ምን ዓይነት አደረጃጀትና አሠራር ይኑረው የሚለውን ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረትና ዩኤስአይዲ በየራሳቸው መንገድ ጥናት እያስጠኑ መሆናቸው ታውቋል፡፡ እነዚህ ጥናቶች ሲጠናቀቁ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚያገኝ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ ባለፉት ዘመናት የቡና ዘርፍ በተለያዩ አደረጃጀቶች ተመርቷል፡፡ ቀደም ሲል ቡና ቦርድ፣ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ቀጥሎም የቡናና ሻይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ የቡናን ዘርፍ ሲመሩት ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ወጥ በሆነ መንገድ ዘርፉን የሚመራ ተቋም ባለመኖሩ ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት መጓዝ ሳይችል እንደቀረ ባለሙያዎች ያብራራሉ፡፡ መንግሥት ዘግይቶ የቡናን ዘርፍ የሚመራ አንድ ጠንካራ ተቋም ያስፈልጋል የሚል ውሳኔ ላይ በመድረሱ፣ ለጉዳዩ ቅ