አሁንም የፕሬስ ነፃነት ይከበር እንላለን!
ሕገ መንግሥቱ ለፕሬስ ነፃነት ዋስትና ሲሰጥ በአንቀጽ 29 በሚገባ በማብራራት በማናቸውም መንገድ ሕጋዊ ከለላ እንደሚደረግለት ደንግጓል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 በሰባት ንዑስ አንቀሶች ታጅቦ የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት አረጋግጧል፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ ወርቃማ አንቀጽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 ቀጥተኛ ግልባጭ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት ማንም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳብ የመግለጽ፣ በፕሬስና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ ማንኛውንም መረጃ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት መብቶችን ያጠቃልላል፡፡ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ተከልክሏል፡፡ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማራመድ ይቻላል፡፡ ለዚህም ሕጋዊ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በእነዚህ መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ ሊሆን ይችላል ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ሥራ ላይ ከዋሉ 22 ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ በማለፍ የግሉ ፕሬስ ውጤቶች ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አይካድም፡፡ አሁንም በጎርባጣው ጎዳና ላይ እየተጓዙ ናቸው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፕሬስ ውጤቶች ይቀርቡባቸው የነበሩ ዓመታት አልፈው አሁን ውስን ጋዜጦችና መጽሔቶች ቀርተዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የግሉ ፕሬስ ፈተናዎች በሁለት ምክንያቶች ሥር ሊጠቃለሉ ይችላሉ፡፡ አንደኛው ውጫዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ውስጣዊ ችግር ነው፡፡ የውጭውን ተፅዕኖ ስንፈትሽ ችግሩ ከመንግሥት ይጀምራል፡፡ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን በተመለከተ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመርያዎችን ከማውጣት ባለፈ ለፕሬሱ ዕድገት የሚያደርገው አስተዋጽ