የገና በዓልና ተያያዥ ኩነቶች
በአገራችን ከሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ገና አንዱ ነው፡፡ ይህ በዓል በክርስትና አማኞች ዘንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መታሰቢያ ነው፡፡ ከፈረንጆቹ ገና በአንድ ሳምንት ዘግይቶ የሚከበረው ይህ ሃይማኖታዊ በዓል፣ በሁሉም የክርስቲያን ቤተ እምነቶች በኩል በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡ የቱሪስት መስህብ በሆነው በደብረ ሮሃ ላስታ ላሊበላ ያለው አከባበር ደግሞ ከሁሉም የተለየና የሚማርክ ነው፡፡ በበዓሉ ዋዜማ ካህናቱ በሚያቀርቡት ኅብረ ዜማ ይደምቃል፡፡ ከላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት አንዱ በሆነው በቤተ ማርያምና በዙሪያው ባለው የማሜ ጋራ ዝማሬው በጥንግ ድርብና በጧፍ ታጅቦ ይከበራል፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንደሚገልጹት፣ በጋራው ላይ የሚያሸበሽቡት ካህናት የመላዕክት፣ ከጋራው ሥር የሚያሸበሽቡት ካህናት ደግሞ የሰው ልጆች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ካህናትና ሰዎች በአንድነት ኢየሱስ ክርስቶስን ያመሰገኑበት ምሳሌ መሆኑ፣ በስፋት ይነገራል፡፡ የገና ባህላዊ በዓልነቱ በአብዛኛው በገጠራማው የአገራችን ክፍል የሚስተዋል ቢሆንም የተወሰኑ የባህሉ ቅሪቶች በአንዳንድ ከተሞችም አይጠፉም፡፡ በዓሉን በባህላዊ ጭፈራ፣ በገና ጨዋታ፣ ባህላዊ ልብስ ለብሶ ማክበር የተለመደ ነው፡፡ ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የሚለው ብሂል እንደሚያስረዳው፣ ሁሉም ወጣት ከቤቱ ወጥቶ በሜዳ ላይ ጨዋታ፣ በደስታና በሃሴት ያከብረዋል፡፡ እንደሌሎች በዓላት ሁሉ በገና በዓል ድፎ መጋገር፣ ሰንጋ መጣል፣ ጠጅና ጠላ መጎንጨት የተለመደ ነው፡፡ እንደ ፈረንጆቹ የበዛ ባይሆንም፣ በዚህ ጊዜ ስጦታ መስጠት የበዓሉ ዓቢይ መገለጫ ነው፡፡ ሕግ የኅብረተሰብን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ትስብር የሚገዛ እንደመሆኑ መጠን እነ