ጥቂቶች ሊመነደጉ፤ ብዙዎች አሽቆልቁለዋል
ከአዲሱ ጠ/ሚኒስትር አዲስ ራዕይ እንፈልጋለን “የራበው ሥራ ፈልጐ ማግኘት የማይችልና ልጆቹን ለማስተማር አቅም ያጣ ሰው ከባርነት ነፃ ነው ማለት አይቻልም፡፡” የሚለው የአሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ሊንደን ቢ. ጆንሰን ንግግር እውነትነት አሁን አሁን በጆሮዬ መደወሉ ራሴን እያስገረመኝ መጥቷል፡፡ የዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት ገደማ ደራሲና ጋዜጠኛ አለማየሁ ገላጋይ፤ ስለኑሮ ውድነት ሲጽፍ ብዙዎቻችን እያነበብን ፈገግ ከማለት በቀር ብዙ ልባችን አልተነካም ነበር፡፡ ምናልባትም በጣም አልፎ አልፎ ከምናነባቸው መጣጥፎች ይልቅ መንግስት ስለ ልማት የሚነፋው ጥሩንባ አደናቁሮን ይሆናል፡፡ አሁን አሁን የመንግሥት መዝገበ ቃላት “ልማት” የሚለው ትርጓሜ ግራ እያጋባን መጥቶ ጭራሽ ወደ ብስጭት የተመነዘረብን ብዙ ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ መንግስት ልማት የሚለው ከእኛ አፍ “ቫት” እያለ የሚነጥቃትን ገንዘብ ሰብስቦ ለሌቦች ካጠገበ በኋላ፣ በፍርፋሪዋ የሚሠራትን መንገድና ጤና ጣቢያ ወይም ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ “ኮንደሚኒየም” እየተባሉ የተሠሩት ቤቶች አካባቢ ያለውን ግድየለሽነት ተመልከቱ፡፡ የውሃ መፍሰሻ ቦዮቹ ገና ተሠርተው ሳያልቁ ይፈርሣሉ። ሕንፃው ውስጥ ያሉትን የግብር ይውጣ ሥራዎች ተውአቸው፡፡ ለመሆኑ ልማትና ዕድገት ምንድነው? ወረቀት ላይ የሃሰት ሪፖርቶችን ከምሮ መቀለድ ነው። ቀልድና ውሸትስ እስከ የት ያዘልቀናል? ከወር ወደ ወር ሰዎች በልተው የማደር አቅማቸውን እያጡ፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ተራራ መቧጠጥ እየሆነባቸው ሲመጣ --- እንዴት ስለ ዕድገት ይወራል? ጋዜጠኛ መሳይ ካድሬዎች ስለልማትና እድገት ብዙ ቢለፈልፉም ከሕዝቡ የበለጠ ጓዳውን የሚያውቅ ማንም ሊኖር አይችልም፡፡ አለ ቢባልም ከተራ ቀልድነት አያልፍም፡፡ እርግጥ ነው፤ ባለፉት ሃያ ዓመታት ጥቂት