ጦጢት ለራሷ ሳትገረዝ፣ የሌላውን ዐይን ትይዛለች
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ ወደ አንድ አሮጊት ቤት ገብቶ ሊሰርቅ አካባቢውን በትክክል ለማጥናት ፈልጐ አንዴ በግራ፣ አንዴ በቀኝ፣ ይሄዳል፡፡ አንዴ በፊት ለፊት፣ አንዴ በጓሮ ይዞራል፡፡ በመጨረሻ ማንም እንደሌለና ማንም እንዳላየው ካረጋገጠ በኋላ ወደ ቤት ዘው ይላል፡፡ ዘወር ዘወር ብሎ ሲያይ፤ ጠባብ አፍ ያለው ማሠሮ ውስጥ እህል አለ፡፡ እጁን ወደማሰሮው ሰደደ። የቻለውን ጨብጦ እጁን ለማውጣት ሲሞክር አልወጣም አለው፡፡ ትንቅንቁን ቀጠለ፡፡ የጨበጠውን እህል ሊተው አልፈለገም፡፡ እንደጨበጠ ላውጣህ ቢለው ደግሞ ጠባቡ የእንስራው አፍ አላሳልፍ አለው፡፡ እንዲሁ ሲታገል ይቆያል፡፡ በሌላ በኩል፤ አሮጊቷ ወንዝ ወርዳ ውሃዋን ቀድታ ስትመለስ፤ መንገድ ላይ ያገኘችውን ሰው ሁሉ ሰላም ትላለች፡፡ ለመጀመሪያው፤ “እንዴት ዋላችሁ?” ትላለች፡፡ “ደህና” ይላል ያገኘችው ሰው፡፡ “ሠፈር ደህና?” “ደህና” “አዝመራ ደህና?” “አዬ ዘንድሮስ እንጃ ዝናቡ ደህና አልሰጠም!” “እንበሶች፣ ላሞች ደህና?” “አዬ ኧረ እንጃ! በሽታው ከፍቷል“ “ሰዉስ ደህና ነው?” “አዬ ሰዉስ ድህነቱን አልቻለውም፡፡” “የእኔ ቤትስ ደህና ነው?” “ኧረ አላወቅንም - የወጣም ሲገባ አላየን፤ የገባም ሲወጣ አላየን” ይላል ሰውዬው፡፡ “ደህና፤ ሁሉን ለደግ ያርገው ይሄን ዓመት!” ብላ መንገዷን ቀጠለች፡፡ ቤት ስትደርስ፤ ያን ሌባ ሳታስተውል፣ የቀዳችውን የቀርበታ ውሃ አስቀምጣ እፎይ አለች፡፡ ከዚያም፤ “አዬ! ይሄ ገደ - ቢስ ዓመት!” አለች፡፡ ይሄን ጊዜ ያ ሌባ፤ “ገደ - ቢሱን ዓመት ተይውና፤ ነይ የእኔን እጅ ከማሠሮው አውጪልኝ!” አላት፡፡ * * * በተረቱ፤ ስለዓመቱ ማማረር ትተሽ ነይ ይልቅ ሥራ ሥሪ፤ ነው ምፀታዊ ትርጉሙ፡፡ ስላቁ ደግሞ የሰው ቤት እየዘ