የሰብዓዊ መብት አፈጻጸምን የሚከልሰው ዕቅድ
ዕውቁ ኖርዌያዊው ተመራማሪ ሼትል ትሮንቮል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን ሪፖርት ተመርኩዞ፣ ‹‹Human Rights Violations in Federal Ethiopia: When Ethnic Identity is a Political Stigma›› በሚል ርዕስ በ2000 ዓ.ም. አንድ የምርምር ጽሑፍ አሳትመው ነበር፡፡ ተመድ በ1999 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም ይከሳል፡፡ ፕሮፌሰር ትሮንቮል በጥናታቸው የተመድ ሪፖርት ድምዳሜ ትክክል እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ጌታቸው አሰፋ ለትሮንቮል በጻፉት የታተመ ምላሻቸው በኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ እንደሚደረግና የመብት ጥሰቱ ክስ ስህተት እንደሆነ፣ ጥሰት አለ ከተባለም ብሔርን መሠረት ያደረገ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደማይፈጸም ተከራክረዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ለንባብ በበቃው ምላሻቸው አቶ ጌታቸው እንደ ሼትል ትሮንቮል ያሉ የውጭ አገር ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ውስብስብ ጉዳዮች በድፍረት ለማሳተም ለራሳቸው ነፃነት የሚሰጡት፡ በአገሪቱ ጥቂት ቀናትን በዛ ካለም ወራትን ካሳለፉ በኋላ መሆኑን ተችተው ነበር፡፡ እነዚህ ተመራማሪዎች በውጭ ጸሐፍት የተጻፉ የምርምር ሥራዎችን ብቻ በማጣቀስ ከባድ ድምዳሜ ላይ እንደሚደርሱም አመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ትሮንቮል ለአቶ ጌታቸው ምላሽ በሰጡት ሌላ ምላሽ ስለኢትዮጵያ ከአቶ ጌታቸው የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ የመመረቂያ ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ እንደነበር ያሰታወሱት ትሮንቮል፣ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምረው በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካና