አባባ ተስፋዬ - በሐዋሳው ተረት ቤት
“ወጣቶች፤ ሀገራችሁን ውደዱ፤ አንብቡ!” በሐዋሳ ከተማ ሐይቁ ዳርቻ በሚገኘው “ሌዊ ሪዞርት” የተሰራው “የተረት ቤት” ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ተመርቋል፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመርያው እንደሆነ የተነገረለት “የተረት ቤት”፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት በሬዲዮና በቴሌቪዥን ተረት በመንገር በሚታወቁት የ90 አመቱ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) ስም የተሰየመ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት የተረት ቤቱ ሲመረቅ በክብር እንግድነት የተገኙት አባባ ተስፋዬ፤ “የጥንቸልና የዔሊ ውድድር” የተሰኘ ታሪክ በመናገር ተረት ቤቱ በይፋ ሥራ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል፡፡ በምረቃው ዕለት ንግግር ያደረጉት የሌዊ ሪዞርት ባለቤት አቶ ወንድይፍራው እንደሻው፤ የተረት ቤቱን መሰራት አስመልክተው ሲናገሩ፤ “የልጆችን የንባብ ልምድ ለማዳበርና በየሳምንቱ ለልጆች ቁምነገር በተረት መልክ የምናስተላልፍበት ነው” ብለዋል፡፡ ተረት ቤቱ ከቢዝነስ ጋር የተገናኘ አይደለም ያሉት አቶ ወንድይፍራው፤ “በውጭ ፊልሞችና ታሪኮች እየተመሰጡ ላሉ ልጆቻችን ታሪካችንን እና ባህላችንን ለማስተላለፍ አስበን ነው” በማለት የተረት ቤቱን ዓላማ ተናግረዋል፡፡ በአዋሳው የተረት ቤት ምረቃ ወቅት የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ከአባባ ተስፋዬ ጋር አጭር ቆይታ በማድረግ የልጅነት ሕይወታቸውን ያስታወሳቸው ሲሆን ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የለቀቁበትን ሁኔታና ዳግም የመመለስ ሃሳብ እንዳላቸው እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አንስቶ ተጨዋውተዋል፡፡ እነሆ፡- በልጅነትዎ ተረት እየሰሙ ነው ያደጉት እንዴ? ተረት አይደለም በልጅነቴ የተነገረኝ፡፡ ቤተሰቦቼ እርግጡን እየነገሩ ነው ያሳደጉኝ፡፡ ቤተሰባችን ለንጉሣውያን ቤተሰብ ቀረብ ያለ ነው፡፡ የተወለድኩት ባሌ አካባቢ ነው፡፡ ጥሩ ነገር ስለመስራት፣ ትእ