ሥልጣን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኦፍ ኬኔዲ ባንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹መጠየቅ ያለብህ አገሬ ለእኔ ምን ሠራችልኝ ብለህ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን ላደርግ እችላለሁ ብለህ መሆን አለበት፡፡›› ይህ የፕሬዚዳንቱ ንግግር በመላው ዓለማችን በበርካቶች የሚታወቅና ጥልቅ መልዕክት የያዘ ነው፡፡ ዛሬ የፕሬዚዳንት ኬኔዲን ንግግር ያነሳነው ስለእሳቸው ለማውራት ሳይሆን፣ ከዚህ ታዋቂ ንግግራቸው ጀርባ ያለውን ቁም ነገር ለመዳሰስ በማሰብ ነው፡፡ በርካቶች በሕይወት ዘመናቸው እንዲኖሩዋቸው ከሚፈልጉዋቸው ነገሮች መካከል አንደኛው ሥልጣን ነው፡፡ ሆኖም ግን በርካታ ሰዎች ሥልጣንን የሚፈልጉት በሥልጣን ውስጥ ያሉ ጥቅሞችን ለማግኘት ካላቸው ክፉኛ መሻት ነው እንጂ፣ በእውነት ሥልጣንን በሚገባ ተረድተውት ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣን ይዞ የሚያመጣቸው በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም፣ ዋነኛ ዓላማው ከዚያ የዘለለ ነው፡፡ ሥልጣን አንድን ነገር ለመግዛት የሚያገለግል ኃይል ቢሆንም፣ ትክክለኛው ትርጓሜው ግን ተገቢ የሆነ ተፅዕኖን በማሳደር ነገሮችን በሥርዓት ለማስጓዝ የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ የምናነሳው ጉዳይ በአገራችን በርካቶች ሥልጣንን የሚጠቀሙት ከምን አንፃር መሆኑን ለመፈተሽ ነው፡፡ በርካቶች የሥልጣንን ትክክለኛ ትርጓሜ ካለማወቅ የተነሳ በአገር እንዲሁም በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ በጊዜው ሃይ ካልተባለ፣ ለባሰ ችግር ማጋለጡ አይቀሬ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በአገራችን ያሉ አንዳንድ ባለሥልጣናትም ስለሥልጣን ምንነት ትክክለኛ ዕውቀት ስለሌላቸው ይህ ነው የማይባል ኪሳራ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሾሙ ልዩ ትኩረት የሚሰጡት በሥልጣን አማካይነት ስለሚገኘው ቤት፣