አገልግሎት አሰጣጥ ሲሳከርና ሲቋረጥ ከመንግሥት ማብራሪያና ይቅርታ ይጠበቃል
በማደግ ላይ ባሉትም ሆነ በበለፀጉት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ፣ የውኃ አቅርቦት መስተጓጎልና የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ያጋጥማል፡፡ መጠኑና ደግግሞሹ በእጅጉ ሊለያይ ይችላል እንጂ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ እያስነሳ ያሉ የአገልግሎት አቅርቦት መሳከርና መቋረጥ እያጋጠሙ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውኃ ለቀናት መጥፋት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ለሳምንትና ለወር ተቋርጦብናል የሚሉ አሉ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በቀን ሦስቴና አራቴ ይቋረጣል፡፡ መደበኛ ስልኮች ይቋረጣሉ፣ ሞባይል ስልኮች አይሠሩም፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎትም ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ የብሮደባንድ፣ የዋይፋይና የኢቪድዮ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የተለመደ ሆኗል፡፡ ለተፈጠሩት ችግሮች ከአቅም በላይ የሆኑና ያልተገመቱ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ግን ቀርበው በግልጽ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ እስኪስተካከሉ ለሚያጋጥሙ የአገልግሎት መቋረጦች መንግሥት ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት የበርካታ ፋብሪካዎች ማሽኖች እየተበላሹና ከባድ ኪሳራ እያስከተሉ ናቸው፡፡ ምርትም እየተቋረጠ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ምክንያት በርካታ የቤት ዕቃዎች እየተቃጠሉና እየተበላሹ ናቸው፡፡ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖችና የኩሽና ዕቃዎች እየተቃጠሉ ቤተሶበችን ለከፍተኛ ኪሳራ እያደረጉ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ፡፡ በዚህ ሰዓት ኢንተርኔት ከፍቼ መልዕክቶችን አያለሁ የሚል ሐሳብ ተረት ተረት እየሆነ ነው፡፡ በዚህም በርካታ የቢዝነስ ሥራዎች እየተስተጓጎሉ ናቸው፡፡ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን በመቋረጡ ምክንያት በርካታ ቢዝነሶች እየተጎዱ ናቸው፡፡ ውኃ፣ ኤሌክትሪክና ስልክ በሌሉበት ሕመምተኞችንና ሕፃና