ከኃላፊነት የተነሱ የቤቶች ኤጀንሲ ባለሥልጣናት ያወጧቸው መመርያዎች ታገዱ
ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በተነሱት ከፍተኛ አመራሮች የሥልጣን ዘመን የወጡ መመርያዎችና የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ትግበራዎች እንዲታገዱ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ የወጡት መመርያዎችና የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች በሙሉ እንዲታገዱ ትዕዛዝ የሰጠው የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስቴሩ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መመርያዎቹ የወጡበት መንገድና የመሠረታዊ የሥራ ለውጡ ተጠንቶ እንዲቀርብለት ጨምሮ አዟል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው መመርያ በማውጣት በኩል ያለው ሥልጣን ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (ቢፒአር) ጥናት የተገበረው ሚኒስቴሩን ሳያማክርና ሚኒስቴሩ ሳያፀድቀው ነው ተብሏል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ፊርማ ከሥልጣናቸው የተነሱት የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ምክትል ሥራ አስኪያጆች አቶ ኃይሉ ሐደሬና አቶ ገብሩ ባይልብኝ፣ እንዲሁም የቤቶች አስተዳደር የሥራ ሒደት ባለቤት የነበሩትና ተቀይረው ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ ኤጀንሲ የተዛወሩት አቶ ኪዳኔ ሥዩም ናቸው፡፡ በእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች የሥልጣን ዘመን ከወጡት መመርያዎች ውስጥ እጅግ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውና እስካሁን ትኩሳቱ ያልበረደው የአከራይ ተከራይ፣ የቤቶች አሰጣጥ፣ የጥገናና ፈቃድ አሰጣጥ መመርያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የአከራይ ተከራይ መመርያ ወጥቶ ተግባራዊ በሆነበት ወቅት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ቀውሶች መፈጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ መመርያ የወጣበት ምክንያት በወቅቱ እንደተገለጸው፣ ከኤጀንሲው ቤቶች የተከራዩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ሸንሽነው ለሌሎች ነጋዴዎች አከራይተዋል፡፡ ይህ አሠራር የኤጀንሲውን ሕግጋት ይፃረራል በሚል ነው፡፡