አስገዳጁ የቁጥጥር ደረጃ ጊዜ ገደብ የግል ጤና ተቋማትን ሥጋት ውስጥ ከትቷል
- ሁኔታውን የሚያጤን ቡድን እየተዋቀረ ነው በኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ተዘጋጅቶ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ 2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የፀደቀው አስገዳጅ የጤና ተቋማት የቁጥጥር ደረጃ ጊዜ ገደብ እንዳሠጋቸው የግል ክሊኒኮች አስታወቁ፡፡ ለአዳዲስ የጤና ተቋማት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ለነባሮች ደግሞ ከፀደቀ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለጸው የቁጥጥር ደረጃ፣ 39 ዓይነት የጤና ተቋማትን መስፈርት ያስቀምጣል፡፡ በመድኃኒት ቁጥጥርና አስተዳደር ባለሥልጣን የቁጥጥር ደረጃ ዝግጅትና አስተባባሪ የሆኑት ሲስተር የሺዓለም በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደረጃው የመንግሥት እንዲሁም የግል ተቋማትንም የሚመለከት ሲሆን ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ የጤና ጣቢያዎችንና ጤና ኬላዎችን ጭምር ያካትታል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከፍተኛ ክሊኒክ የሚባሉት ልዩ የሕክምና ማዕከላት (Specialty Center) መሆን የሚችሉ ሲሆን፣ ለዚህ በትንሹ አሥር አልጋዎች፣ ሁለት ስፔሻሊስት ሐኪሞች እንዲሁም ፋርማሲ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህን ማሟላት ካልቻሉ ደግሞ ሁለት ወይም ሦስት የተመላላሽ ታካሚ አልጋ ኖሯቸው በአንድ ስፔሻሊስት ሐኪም አጠቃላይ አገልግሎት የሚሰጥ መካከለኛ ጤና ተቋም መሆን ይችላሉ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያሉ ማሟላት እንደሚችሉ የመስፈርት አማራጮች ተቀምጠዋል፡፡ ክሊኒኮች የባለሙያ እጥረትን እንዲሁም የቦታ ጥበትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያሰሙ ሲሆን፣ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከፍተኛ ክሊኒክ ባለቤት “ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የቻልነውን ያህል መስፈርቶቹን አሟልተን ለመቀጠል እንሞክራለን ካልሆነ ግን እንዘጋለን፤” በማለት ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተ