ኢኮኖሚውን ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚያሳድገው በጀት ለፓርላማ ቀረበ
- ሚኒስትር ሱፊያን ለመጀመርያ ጊዜ ጠንካራ ቁጥጥር ገጠማቸው -ለመንገድ 29.1 ቢሊዮን ብር ለመከላከያ 7.5 ቢሊዮን ብር ተይዟል የኢትዮጵያን አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ወደ አንድ ትሪሊዮን ብር የሚያደርሰው የ2006 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ በጀቱን ያቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ ከፓርላማው ጠንካራ ቁጥጥር ገጥሟቸዋል፡፡ ሚኒስትሩ የአገሪቱን የዓምናና የዘንድሮ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጥሩና በአስደሳች ሁኔታ ውስጥ መሆኑን፣ እንዲሁም ያሉበትን ፈታኝ ችግሮች በቅድሚያ በመዳሰስ ያለውን በጎ ኢኮኖሚያዊ ሒደት ለማጠናከርና ችግሮችን ለመቅረፍ ለተወጠኑ ግቦች ይረዳል ያሉትን የ2006 ዓ.ም. ረቂቅ በጀት አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት የአገሪቱ የቀጣይ ዓመት በጀት 154 ቢሊዮን 903 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ከዚህ ውስጥም 32.53 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 64.32 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ፕሮጀክቶች፣ 43.05 ቢሊዮን ብሩ ለክልል መንግሥታት ድጎማ፣ እንዲሁም ቀሪው 15 ቢሊዮን ብር ለምዕተ ዓመቱ ግቦች ማጠናከሪያ ወጪዎች መሸፈኛ እንደሚውል አብራርተዋል፡፡ የተጠቀሰው የቀጣይ ዓመት ረቂቅ በጀት ከዘንድሮው ጋር ሲነፃፀር በ12.3 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከረቂቅ በጀቱ ውስጥ ከፍተኛውን የ41.5 በመቶ ድርሻ የያዘው የፌዴራል መንግሥት የካፒታል ፕሮጀክቶች ወጪ ነው፡፡ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተመደበው 64.32 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው ነባር ፕሮጀክቶች እንዲሆኑ የተወሰኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ብቻ እንዲካተቱ በማድረግ፣ ከአገሪቱ የገንዘብ አቅም ጋር እንዲጣጣም መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ የተጠቀሰው የካፒታል ፕሮጀክቶች በጀት ከዘንድ