ልቅሶ የተካው የእልልታ ቀን
‹‹የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ቅነሳ በተመለከተ እ.ኤ.አ በ2015 እናሳካዋለን ያልነውን የሚሌኒየሙን ግብ አሁን በያዝነው አሠራር የምንቀጥል ከሆነ ግቡ ጋር ለመድረስ ተጨማሪ 150 ዓመት ያስፈልገናል፡፡›› ይህንን የተናገሩት የሕፃናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) የኦፕሬሽን ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ኃይሉ ተስፋዬ ናቸው፡፡ ሁለት ዓመት ከሰባት ወር ገደማ ከቀረው ከሚሌኒየሙ እቅዶች መካከል አንዱ የሕፃናትና የእናቶች ሞት ቅነሳ ነው፡፡ ዶክተር ኃይሉም ግቡን ለማሳካት አሠራሮች ይቀየሩ የሚለውን ሐሳባቸውን ያንፀባረቁት፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሑድ በሐዋሳ ከተማ በተደረገው የ‹‹ሁሉም›› የእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ ዘመቻ ላይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ይሳካል የተባለለት ትልቁ ዕቅድ ጨቅላ ሕፃናት በተወለዱ በ24 ሰዓታትና በተወለዱ በመጀመርያዎቹ ሰባት ቀናት ውስጥ ተገቢው ክትትል ካልተደረገላቸው መሞታቸው ቀጥሎ ግቡም አይሳካም፡፡ በዚህ አሠራር ከተቀጠለ ግን ግቡን ለማሳካት እ.ኤ.አ 2165 ድረስ መቆየት ግድ እንደሚል ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡ የእናቶችን ሞት መቀነስን በተመለከተ ደግሞ የቤተሰብ ምጣኔ፣ የእርግዝና ክትትል፣ የወሊድና ከወሊድ በኋላ የሚደረግ ክትትልና እንክብካቤ ከመቼውም በላይ የሚሠራባቸው ከሆነ የሚሌኒየሙን ግብ ማሳካት እንደሚቻል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የ‹‹ሁሉም›› ዘመቻ የእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳን ለማሳካት በዘመቻ መልኩ በሕፃናት አድን ድርጅት ሥር ከተመሠረተ አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ በ36 አገሮች በየዓመቱ እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ዘመቻ፣ የእናቶችና ሕፃናት ሞት የሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ማኅበረሰቡን በዘመቻው አነሳስቶ የሞቱን ቅነሳ ለማድረግ ጥረት የሚደረግበት ፕሮግራም ነው፡፡ የሕፃናት