ኢኮኖሚውና ቢዝነሱ ፈዟል! እናነቃቃው እንጂ!
ኢኮኖሚው ወድቋል፣ ሞቷል አይደለም እያልን ያለነው፡፡ ፈዟል ነው፡፡ በእውነት ፈዟል፡፡ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ፣ ተግባር ላይ ሲውሉና ሲሳኩም አገርን በእጅጉ የሚጠቅሙ፣ በሐሳብና በፍላጎት ብቻ ሳይሆን በተግባር ሥራቸው የተጀመረ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በሚያስተማምን ሁኔታ በቂ በጀት እያገኙ ያሉ ፕሮጀክቶች አይደሉም፡፡ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ከተገኘ ጥሩ፣ ካልተገኘ ደግሞ ራሳችን እንፈጽማቸዋለን ብለን የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በራስ ተማምኖ መጓዝን የመሰለ የለም፡፡ እዚህ ላይ ስህተት የለም፡፡ ነገር ግን በራስ መተማመን በራስ ገንዘብን እውን ከማድረግ ጋር መያያዝ አለበት፡፡ ምርት እያደገ፣ ኤክስፖርት እያደገ፣ ግብር እያደገ፣ ወዘተ ሲሄድ ነው የውስጥ አቅም ሊጨምር የሚችለው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዕድገትና የአቅም መጎልበት ካልታየ ሊገኝ የታሰበው በጀት ላይገኝ ስለሚችል በዕቅዶች ላይ መጓተት ያስከትላል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶች በቂ በጀት እያገኙ አይደሉም፡፡ የምድር ባቡር ሥራው በበጀት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ አይደለም፡፡ መንግሥት ከግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶችና ከሌሎች ዓበይት ሥራዎችን ከሚሠሩ የግል ድርጅቶች ጋር ተዋውሎ ላሠራው ሥራ ለመክፈልም ሲቸገር እየታየ ነው፡፡ ሥራው ተሠርቷል ክፍያ ግን አልተፈጸመም፡፡ ሁሉም ችግር በገንዘብ ባይመካኝም የገንዘብ እጥረት አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በተገቢው ደረጃ ብድር እየሰጡ አይደሉም፡፡ ያላግባብ የሚሰጥ ብድርን ማረምና ማስተካከል ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እየታየ ያለው ችግር ጉድለትን የማስተካከል ሳይሆን ለተገቢው ብድር ብቁና ንቁ ሆኖ አለመገኘት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይም እንደዚሁ አስተማማኝ አይደለም፤ እጥረት አለበት፡፡ ሙስናም አለበት፡፡ የአቅም ማነስም አለበት፡