ኢህአዴግ በሁሉም የምርጫ ቦታ አሸንፌያለሁ ይላል
በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አሸንፈናል” - ተቃዋሚዎች ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የከተማ ምክር ቤቶች ምርጫ ኢህአዴግ ጊዜያዊ ውጤት በመጥቀስ በሁሉም ቦታዎች እንዳሸነፈ የገለፀ ሲሆን በምርጫው የተሳተፉ ተቃዋሚዎች በውጤቱ እርግጠኛ ባይሆኑም በጥቂት የአዲስ አበባ ምክር ቤት ቦታዎች የምናሸንፍ ይመስለናል ብለዋል፡፡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ “ህዝቡ ጥሩ ድምጽ እንደሰጠን እናውቃለን፡፡ ውጤቱን በተመለከተ ግን የምርጫ ቦርድ ይፋ ካደረገ በኋላ የምናየው ይሆናል” ብለዋል፡፡ አቶ አየለ አክለውም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች እጩዎቻቸው አሸናፊ እንደሆኑ ነገር ግን የመጨረሻውን ውጤት በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የሚወሰን ስለሚሆን የምርጫ ቦርድ መግለጫ መጠበቅ የግድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ አየለ በሂደቱ ላይ የታዩ ብዙ ችግሮች እንደነበሩ ገልፀው፣ ከነዚህ መካከል የንብ ምልክት ብቻ በየጣቢያው መቀመጡ እንዲሁም በድምጽ ቆጠራ ወቅት የእነሱ ታዛቢዎች እንዳይገኙ መደረጋቸው ተገቢ አይደለም፤ ቅሬታችንን በወቅቱ ለምርጫ ቦርድ አቅርበናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፣ በምርጫው ውጤት እንዳልቀናቸው ማረጋገጣቸውን ጠቅሰው፣ ፓርቲያቸው በምርጫው መሳተፉን ይበልጥ ከህብረተሰቡ ጋር እንዲተዋወቅ እንዳደረገው ገልፀዋል፡፡ የምርጫው አጠቃላይ ሂደትና ውጤት በተመለከተ ያላቸውን አቋምም በምርጫ ቦርድ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ እንደሚያሳውቁ አቶ ተሻለ ገልፀዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ሊቀመንበር አቶ መሣፍንት ሽፈራው፤ በአዲስ አበባ በሶስት የምርጫ ጣቢያዎች ቢያሸንፉም አጠቃላይ ውጤቱን ለማወቅ የምርጫ ቦርድን መግለጫ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ በበኩሉ በአዲስ