‹‹በሕዝብ የተመረጥኩ ነኝ›› ብሎ የሚያምን መንግሥት ‹‹ሕዝብ አለቃዬ ነው›› ብሎ ማመንም አለበት
ሕገ መንግሥታችን ሥልጣን የሚይዝ መንግሥት በሕዝብ ድምፅ ብልጫ የተመረጠ መሆን አለበት ይላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉድለት አለው እንዲህ መሰል ችግር ነበረው ቢባልም፣ በተግባር ምርጫ የሚካሄድበት አገርና ሕዝብ ሆነናል፡፡ ምርጫ በማካሄድ መንግሥትን ሥልጣን ላይ ማስቀመጥ ማለትና ለገዥው ፓርቲ ሕዝባዊ ድምፅ ሰጥቶ በአመራር ላይ ማስቀመጥ ማለት ግን በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት የማኖር ተግባር ነው፡፡ ኃላፊነቱም ሕዝብን በግዴታም በውዴታም የማገልገል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ መንግሥትን የሚመርጠው፣ አመራርን የሚመርጠው፣ አስተዳደርን የሚመርጠው ‹‹አገልግለኝ›› ብሎ ነው፡፡ ስለሆነም በሕዝብ ተመርጦ ሥልጣን ላይ የተቀመጥኩ መንግሥት ነኝ የሚል ገዥ ፓርቲ አለቃዬ የመረጠኝ ሕዝብ ነው በማለት ማመን አለበት፡፡ በሕዝብ መመረጥ መብቴ ነው የሚል ገዥ ፓርቲ ሕዝብን ማገልገል ግዴታዬ ነው ብሎም ማመን አለበት፡፡ ሕገ መንግሥታችንም ያስገድደዋል፡፡ ሕዝብ አለቃዬ ነው፣ ሕዝብን ማገልገል ግዴታዬ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥት ደግሞ የሕዝብን ጥያቄ ይመልሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ እንደ ገዥ ፓርቲ ራሱን መጠየቅ፣ መፈተሽና መገምገም ያለበት በእውነት የሕዝብን ጥያቄ እየመለስኩ ነው ወይ? ብሎ ነው፡፡ ሕዝብ መልካም አስተዳደር እንዲኖር እየጠየቀ ነው፡፡ ሕዝብ እንደ አለቃ መንግሥትን ሥልጣን ላይ ያስቀመጥኩህ መልካም አስተዳደር እንድታመጣልኝ ነው፡፡ የት አለ መልካም አስተዳደሩ እያለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደፈር ብሎ አዎን ሕዝብ ሆይ የሚገባኝን መልካም አስተዳደር ስላልሰጠሁህ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ አሁን ግን አሟላለሁ ማለት አለበት፡፡ የት አቤት እንደሚባል እየጠፋ ነው፡፡ መልስ ሰጪ እየታጣ ነው፡፡ እንባ ሲፈስ እንጂ ሲታበስ አይ