ለኢቴቪ ዓመቱን ሙሉ “April the fool” ነው!
ሰሞኑን የተከሰተ ዜና ነው - እዚህ ሳይሆን ፈረንጆቹ አገር፡፡ ሁለት ታዳጊ ፍቅረኛሞች ናቸው አሉ፡፡ የፍቅር ጓደኝነት ከመሰረቱ ብዙ አልቆዩም፡፡ ግን ሲዋደዱ ለጉድ ነው፡፡ (እንደ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች እንዳትሉኝ!) ባለፈው ሰኞ ግን በጨዋታ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት እሷ እሱን አንገቱ ላይ በስለት ወግታው ወህኒ ወረደች አሉ (የአፍሪካ ፖለቲካ አይመስልም?) አያችሁ እንዲህ በጨዋታ መሃል ያልተጠበቀ አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡ አንዳንዴ ዓይን ሊጠፋ ወይም እግር ሊሰበር ይችላል፡፡ ባስ ሲል ህይወትም ይጠፋል፡፡ በፍቅር ጨዋታ እንዲህ ካጋጠመ በፖለቲካ ጨዋታ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል አስቡት፡፡ እቺን እቺንማ ከእኛ በላይ ማን ያውቃታል? ምንም ቢሆን እኮ የአፍሪካ ልጆች ነን! (የአራዳ ልጅ እንዲሉ) የጨዋታው አባቶች የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ከሆኑ ደግሞ ነገርዬው የከፋ ይሆናል - የመረረ!! ለምን መሰላችሁ? መቼ እንደሚያመሩ፤ መቼ ከፍቅር ወደ ጥላቻ እንደሚሸጋገሩ ፈጽሞ አታውቁም፡፡ ኳስ ይዞ የነበረው እጃቸው በምን ቅጽበት ጠብመንጃውን አፈፍ እንዳደረገ ፈጣሪያቸው ብቻ ነው (የራሳቸው ፈጣሪ ይኖራቸዋል ብዬ እኮ ነው!) የሚያውቀው (“አድነነ ከመዓቱ” ማለት ይሄኔ ነው!) ይኸውላችሁ የእኔ ነገር የፍቅረኞቹን ሳልጨርስላችሁ ፖለቲካ ውስጥ መሰስ ብዬ ገባሁላችሁ፡፡ (ፖለቲካ አሳሳች እኮ ነው!) እናላችሁ.. ሁለቱ ፍቅረኛሞች ሲገናኙ ሁሉም ነገር አማን ነበር፡፡ በተለይ እሱ ፍቅር እንጂ ሌላ አልጠበቀም፡፡ እሷም ብትሆን ያለወትሮዋ ቀልድና ጨዋታ አምሯታል እንጂ ሌላ ነገር አላሰበችም፡፡ በጨዋታቸው መሃል ግን አንድ ዱብዕዳ ዜና ጣል አደረገችበት - እንደዘበት! “አርግዣለሁ” አለችው፡፡ “What?” (ምን? ትቀልጃለሽ? አብደሻል? ወዘተ… ሊል እንደሚችል ገምቱ!) ፍቅረ