“ኢህአዴግ ጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ ለማግኘት አልታደለም”
በግጥም ምሽቶች መታደም ትልቅ ደስታ ይሰጠኛል------ ኢህአዴግ ለተቃዋሚዎች ድጋፍ ነፍጓል ብዬ አላስብም----- ኢትዮጵያ ከፓርቲዎች ፖለቲካ በላይ ልትወሰድ ይገባል----- አቶ ህላዌ ዮሴፍ በብአዴን መስራችነታቸው፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ድርጅቱ ለቅስቀሳ ይጠቀምባቸው የነበሩትን መዝሙሮች ግጥምና ዜማ በመድረስ እንዲሁም በበርካታ ቀስቃሽና ወቅታዊ የግጥም ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ የአማራ ልማት ማህበርን (አልማ) ለሃያ አመታት በሥራ አስኪያጅነትና በቦርድ ሊቀመንበርነት አገልግለዋል፡፡ በአምባሳደርነት ተመድበው ከሚሰሩበት እሥራኤል አገር ፤ ለብአዴን ድርጅታዊ ስብሰባና ለዘጠነኛው የኢህአዴግ ጉባዔ ወደ አገራቸው በመጡበት ወቅት ከጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ጋር በባህርዳር ከተማ ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ ብአዴን በቅርቡ ባካሄደው ድርጅታዊ ስብሰባ ወቅት ያደረገው መሰረታዊ ለውጥ አለ? በድርጅቱ ውስጥ በፖሊሲ፣ በፖለቲካ አቋምና መስመሮች ዙሪያ የተደረገ ለውጥ የለም፡፡ በአመራር ደረጃ ከነበሩት 65 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል 20 የሚሆኑትን ቀይረናል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሌም በጉባኤው ወቅት የሚከናወን ጉዳይ ነው፡፡ በተረፈ ድርጅቱ በሥራ አፈፃፀሙና አባላቱን በማጠናከሩ ረገድ ራሱን እያሻሻለ መሄዱንና በአስተማማኝ ጥንካሬ ላይ መድረሱን አረጋግጠናል፡፡ በአንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ መሻሻልና መስተካከል ይገባቸዋል ያልናቸውን ጉዳዮችም አንስተን ተወያይተናል፡፡ በመልካም አስተዳደር ረገድ በፌደራል ደረጃ በተደጋጋሚ እንደሚነሳው፣ በአማራ ክልልም አንዳንድ ትኩረት ሰጥተን ልናያቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉም አይተናል፡፡ በእኔ አስተያየት ድርጅቱ በጤናማ አቅጣጫ እየተጓዘ ነው፡፡ ስለመጪው ምርጫ ምን አስተያየት አለዎት? ኢህአዴግ ምርጫውን ህዝብ የሚያምንበት ምርጫ ያደርገዋል