መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የቅስቀሳ ፕሮግራም በተገቢው መንገድ ሊያስተናግዱ ይገባል
አዲስ አበባ የካቲት 27/2005 መገናኛ ብዙሃን በ2005 ዓ.ም ለሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የቅስቀሳ ፕሮግራም በተገቢው መንገድ እንዲያስተናግዱ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመጪው መጋቢት 4 ቀን እስከ ሚያዚያ 4/2005 ድረስ ለሚያቀርቡት የምርጫ ቅስቀሳ የሬዲዮና የቴሌቪዥን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል በዕጣ ተከናውኗል፡፡ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ልዑል ገብሩ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት መገናኛ ብዙሃን ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን የቅስቀሳ ፕሮግራም ህግና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት በአግባቡ ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ድልድሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባፀደቀው መመሪያ መሰረት መከናወኑንና 50 በመቶ ሁሉም ፓርቲዎች በእኩል የሚካፈሉት ሆኖ 30 በመቶ በሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች ባላቸው ብልጫ፣ 20 በመቶውን ጊዜ ደግሞ ባቀረቡት እጩ ተወዳዳሪ ብዛት የሚጠቀሙ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሰረትም 24ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሬዲዮ 19 ሠዓት ከ20 ደቂቃ፣ በቴሌቪዥን 12 ሠዓትና በተለያዩ ጋዜጦች 48 አምዶችን ያለምንም ክፍያ የምርጫ ቅስቀሳቸውን እዲያካሂዱ መደልደሉን ተናግረዋል፡፡ ለዚሁ ስራ የተመደበው የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ በገንዘብ ሲተመን ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያህል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ይህም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፖሊሲያቸውን፣ ስትራቴጂያቸውንና ፕሮግራማቸውን ለህብረተሰቡ በነጻነት እንዲያቀርቡ መንግሥት ካለው ቁርጠኝነት አንጻር የተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች ልምድ እንደታየው የተመደበላቸውን የአየር ሠዓትና የጋዜጣ አምድ ያለመጠቀም ችግር መታየቱን ያስታወሱት አቶ ልዑል ፓርቲዎች የተሰጣቸውን እ