ትክክለኛ አስተሳሰብ ሲኖርህ ትክክለኛ ሰው ትሆናለህ
ለቃላት ትክክለኛና ጥርት ያለ ትርጉም ለመስጠት ብሎም የቃላትን ብዥታና (vagueness) አሻሚነትን (ambiguity) ለማስወገድ ለእያንዳንዱ ቃል በተለያየ አውድ ውስጥ የሚኖረውን ብያኔ በትክክል መረዳትና እያንዳንዱንም ቃል በተገቢውና በትክክለኛ ቦታ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ የቋንቋ ፍልስፍና ሊቃውንት ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ “ደረቅ እንጀራ አለ” እና “ለምለም እንጀራ አለ” የሚሉትን በአዲስ አበባ እና በሐዋሳ ከተሞች የተለመዱ ሁለት የእንጀራ ሽያጭ ማስታወቂዎችን የቃላት አጠቃቀም ትክክለኝነትን ብናነጻጽር “ደረቅ እንጀራ” የሚለው ቃል “ድርቆሽ እንጀራ” የሚለውንም ትርጉም በውስጡ ስለሚይዝ የበለጠ አሻሚ (ambigious) ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የእስራኤሉ ንጉስ ዳዊት የሚሞትበት ቀን በቀረበ ጊዜ ልጁ ሰሎሞንን ያዘዘው ዋነኛ ትእዛዝ “ሰው ሁን” የሚል እንደነበር በመጽሐፈ ነገስት ቀዳማዊ እናነባለን፡፡ ሰው ሆኖ ከተፈጠረ በኋላ ሰው ሁን ተብሎ መታዘዙ ሰው መሆን በስጋና በደም ጸንቶ ከመንቀሳቀስ የዘለለ መለኪያ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው” ሲል ደግሞ አንዱ መስፈሪያ ማሰብ (thinking) መሆኑን ይመሰክራል፡፡ “ማሰብ የሰውነት መገለጫ ነው” በሚለው ዓረፍተ ነገር የተስማማ ሰው “ትክክለኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ደግሞ ትክክለኛ ሰው ነው” የሚለውን ዓረፍተ ነገር እውነትነትም በአመክንዮ መርህ መቀበል ይኖርበታል፡፡ በርግጥም ሁሉም ሰዎች ማሰባቸው እውነታ ቢሆንም ሁሉም ሰዎች በትክክል ማሰባቸው ግን በጥያቄ ምልክት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም በህጸጽ የተሞላ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች ህጸጾቻቸውንና የተሳሳተ ድምዳሜያቸውን በየደቂቃው በንግግራቸውም ሆነ በጽሁፋቸው ሲገልጹ ይስተዋላሉና