ዜጎችን አሳንሶ ራሱን ያገዘፈው “ልማታዊ መንግስት”
“የምትፈልገውን ሁሉ እሰጥሃለሁ የሚል ግዙፍ መንግስት ያለህን ለመውሰድም ግዙፍ አቅም አለው” እንደ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያሉ ግራ ዘመም የቡድን መብት አቀንቃኞች፤የዜጎችን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎ አሳንሶና ገድቦ ሚናቸውን በመንግስትና በተቋማቱ በመተካት ግዙፍ መንግስትና ጉርድ ዜጋ መፍጠር የፍልስፍናቸው መሰረት ነው፡፡ ምርጫው ነጻና ገለልተኛ ሆነም አልሆነም ወቅቱን የጠበቀ ምርጫ ለሚያካሂዱ አብዮታዊ ዴሞክራቶችና “ልማታዊ መንግስታት”፤በስልጣን ላይ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ለመቆየት ፖለቲካውን መምራትና መቆጣጠር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ “ልማታዊ መንግስታት” መንግስታዊ ተቋማትን ተጠቅሞ የኢኮኖሚውና የተፈጥሮ ሃብቱ ማዕከል በመሆን የስራ እድል ፈጣሪ፣ ሃብት አቅራቢ፣የሃብት ፈጠራ ምንጭና መንስኤ ብሎም አከፋፋይና አደላዳይ መሆን ለሕልውናቸው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ የህዝብ ተሳትፎ ባለበት ከባቢያዊ ሁኔታ ምኞትን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስፈልገው የፈጣሪነትና የአድራጊነት አቅም በቂ ስለማይሆን፤የማይናወጥ፣የማይበረዝና የማይከለስ (ካህሌ ኩሉ) አቅም ለመንግስትና ለተቋማቱ ማቀዳጀት አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሊብራል ዴሞክራሲ ፍልስፍና፤በዜጎች እኩልነትና ነጻነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሊብራል ዴሞክራሲ ዜጎች በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ለሚኖራቸው አይተኬ ሚና ልዩ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ በሚኖራቸው ተሳትፎ ልክ የሃገርን ኢኮኖሚያዊ አቅም ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በማጎልበት የስራ እድል ፈጠራን በማስፋፋት፣ለሃገር ልማትና እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በመንግስትም ሆነ በተቋማቱ እንዳይተካ ፍጹም የሆነ ከለላ ይሰጣል፡፡ በፖለቲካው ዘርፍም ቢሆን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች