ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የመንግሥት ፕሮጀክት ግዥዎችን እመረምራለሁ አለ
- ስዊስ ባንክ በታምራት ላይኔ ስም የተቀመጠ ስምንት ሚሊዮን ዶላር መለሰ በውድነህ ዘነበ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ከሚያካሂዷቸው ግዥዎች ጋር በተያያዘ የሙስና ሥጋት በመፈጠሩ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ እጀምራለሁ አለ፡፡ ኮሚሽኑ ምርመራ ከሚያካሂድባቸው ፕሮጀክቶች መካከል በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት የሚካሄዱ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የሚካሄዱ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦችና ጣቢያዎች ግንባታና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚካሄዱ ትላልቅ የኢንጂነሪንግ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ በትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲያተኩር መመርያ ተሰጥቶታል፡፡ “ቀደም ሲል ከምናካሂደው በተለየ ሁኔታ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግዥ ላይ እናተኩራለን፤” ሲሉ አቶ ዓሊ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ በመቶ ቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ በርካታ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ መሰማራቱ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ግዙፍ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ እየተዘጋጀ ያለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለምርመራው ያለውን የሰው ኃይል እንደሚያሰማራ ተገልጿል፡፡ ጥቃቅን የሙስና ወንጀሎችን እንጂ ታላላቅ ሙስናዎች አይደፍርም በሚል የሚታማው ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ዘግይቶም ቢሆን በእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ምርመራ ለመጀመር መዘጋጀቱ መልካም ነው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሽግግሩ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና የመከላከያ ሚኒስትር ከነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ወዲህ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሙስና ባለመጠየ