ሹመት ችግር ካልፈታ ፋይዳ ቢስ ነው!
ሰላም! ሰላም! ለዛና ጨዋታ ናፈቀን አይደል ጎበዝ? የድርቅ ታሪካችንን ለማጥፋት ስንረባረብ ሳይታወቀን የጨዋታ ድርቅ እየወረሰን መጣ መሰለኝ። የሚወራው፣ የሚሰማው፣ የሚዘፈነው፣ የሚታየው ሁሉ ለዛ በማጣት ድርቅ ከተመታ ምን ይውጠናል? እንዴ መኖር እየጠላን እንዴት እንዘልቃለን? እውነት እውነት ስላችሁ! ሳቅና ጨዋታ ከአታካቹ ኑሯችን ከተባረረ መሀል ላይ ስንዋልል ጥሩ አይመስለኝም። ‹‹አይ አንተ ሁሌም አንድ ሐሳብ አያጣህም?›› አለችኝ ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹ሳቅ አላማረሽም?›› ብዬ ብጠይቃት። በነገራችን ላይ ማንጠግቦሽ ከት ብላ ከሳቀች ድንበር ተሻጋሪ ድምጿን ማንም ነው ሚሰማው። አሁን ታዲያ በገባሁ በወጣሁ ቁጥር ‹‹ምነው ሰላም አይደላችሁም?›› የሚለኝ ሠፈርተኛ በዝቷል። ይኼኔማ አንዳንዱ ተጣሉም ብሎ ያስወራ ይሆናል። ሰው እንዴት የሰውን ጓዳ ጎድጓዳ እየተከታተለ እንደሚኖር ሳስብ በእጅጉ ይደንቀኝ ጀመር። በነገራችን ላይ ከመሬት እየተነሳ ባለፀጋ የሚሆነው አልበዛባችሁም? መጠቃቀም በሕዝብ ሀብት ባይሆን ጥሩ ነው እያልን ብንመክር ብናስመክር ማን ከመጤፍ ቆጠረን? ‹‹ምርጫ ሲደርስ ብቻ የሚቆጠረው ድምፃችን ከወዲሁ ሰሚ ቢያገኝ ኖሮ የሌባው ቁጥር እንዲህ ባልበዛ ነበር፤›› ይለኛል የባሻዬ ልጅ በአንድ ጀንበር የሚከብሩ ሲበዙበት። መክበራቸው ሳያንስ ተፈርተው መኖራቸው የሚያበሳጨን አደባባይ ይቁጠረን። እናም ሳቅ ጠፋ የምለው በየትኛውም ሥፍራ እያረሩ መሳቅ የደስታ ምልክት ነው ተብሎ ስለማይቆጠር ነው። ለነገሩ ዝም ብላችሁ ብትታዘቡ እንኳን መሳቅ ይቅርና እሪ ብሎ ማልቀስስ ተወዷል። (ቆይ የማይወደደው ምን ይሆን?) ‹‹ይኼ ለብ ማለት ደግ አይደለም አንበርብር፤›› ይሉኛል ባሻዬ ጋቢያቸውን እያጣፉ። ኑሯችን ከአንዱ ወደ አንዱ እንደኳስ እየጠለዘ ሲጫወትብን መሳቅ