አማራጭ ሐሳብና አማራጭ ጥንካሬ ያለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ይፈለጋል!
አገራችን ኢትዮጵያ ምን እንድትሆን ትፈልጋላችሁ ብንባል ቀጥተኛውና ቀልጣፋው መልሳችን የበለፀገችና ዲሞክራሲያዊት አገር እንድትሆን እንፈልጋለን ነው፡፡ ልማትና ዲሞክራሲ ጐን ለጐን ተያይዘውና ተሳስረው የሚታዩባት አገር እንድትሆን እንፈልጋለን፡፡ ልማት እንጂ ዲሞክራሲ አንፈልግም የሚለውን አንቀበልም፡፡ ዲሞክራሲ እንጂ ልማት አንፈልግም የሚለውንም አንቀበልም፡፡ ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ መንግሥትና ፖለቲካ እንፈልጋለን፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንፈልጋለን ስንል አንዱ መገለጫው የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት እውን ማድረግ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም የተሻለ ሐሳብ አለን የሚሉ ኃይሎች የሚሰባሰቡበትና የሚደራጁበት የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠርና ሥልጣን ለመያዝ መወዳደር መብት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥርዓት እውን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ሐሳቦች እርስ በርስ ይወዳደራሉ፤ ይታገላሉ፡፡ ሕዝቡም የተሻለውን ሐሳብ ይመርጣል፡፡ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠውም አገሪቱን እንዲመራ ኃላፊነት ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ሕዝብም፣ መንግሥትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሥነ ሐሳብ ደረጃ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሕዝብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኖረው ይወዳደሩ ብሎ ያምናል፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሰፍሯል፡፡ በተግባር ግን የጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ትግል፣ ፉክክርና ውድድር ማየት አልቻልንም፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆነው ጠንካራ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በተግባር በኢትዮጵያ እውን መሆን አልቻለም፡፡ ለምን? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ መሆን ያልቻልነው ገዥው ፓርቲ እንዳንጠናከር ስላደረገን ነው የሚል መከራከሪያ ሊ