አሞራ ገደልና የዓሳ ገበያው
በሔኖክ ረታ ቀደም ሲል አካባቢውን ለሚያውቀው ጎብኚ የአሞራ ገደል አሰያየም በቀጥታ ከአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ ጋር ስለመዛመዱ መናገር ይችላል፡፡ ከከተማዋ ፈጣን ዕድገትና በየአቅጣጫው ከተስፋፋው የሥራ ዕድል ጋር ተያይዞ ግን ለከተማዋ ጀባ የተባለው ትኩረት ለዚህም የሐይቁ ታዋቂ ስፍራ እንደ ፀበል ደርሶ በመጠኑም ቢሆን የአጥር መከለያ ተሠርቶለትና ከዚህ በፊት እዚህም እዚያም ይጠባበስ የነበረው የዓሳ ምግብ በወጉ እየተዘጋጀ ለተመጋቢው መቅረብ ጀምሯል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ይህ ዝነኛ የሐይቁ ክፍል አሁንም ቢሆንም እንደሌላኛው የሐይቁ መዳረሻ በሰንደቅ ዓላማና በቀለማት ባሸበረቁ ጀልባዎች፣ አበቦችና የማስታወቂያ ሰሌዳዎች የደመቀ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዓሳ ጎርጓሪ ወፎች፣ እነ አባ ኮዳ፣ አባጆፌዎችና ሌሎቹም ዓሳ ተመጋቢ ወፎች እንደትናንቱ ግቢውን ወረው፤ ከዓሳ አጥማጆች የሚያፈተልኩትን ጥቃቅን ዓሶችንና ከበላተኛው ተርፈው የተጣሉ ትርፍራፊዎችን እየተሻሙ ሲለቅሙ የሚታዩበት እንጂ፡፡ ለሁለት በተከፈለው ሰፊ ግቢ በአንደኛው በር የመግቢያ ትኬት እየተቆረጠበት በፓርክ (መናፈሻ) ውስጥ ፎቶግራፍ ለመነሣት የሚቻል ሲሆን በሌላኛው በር ደግሞ የዓሳ ጥብስና ሾርባን ለመመገብ ብቻ ታስቦ በነፃ የሚስተናገዱበት በር ይገኛል፡፡ በዚህ በር በስተግራ በኩል መደዳውን እንደ ሱቅ የተደረደሩት ደሳሳ ቤቶች እንደዋዛ በደረደሯቸው የመመገቢያ ጠረጴዛና ወንበሮች ተኮልኩሎ ለሚጠብቃቸው ተመጋቢ ፊሌቶ የተሰኘውን የአካባቢውን ተወዳጅ ዓሳ የሚጠበስባቸውና ሾርባው የሚዘጋጅባቸው ኩሽናዎች ናቸው፡፡ ‹‹ኧረ እባካችሁ! ቆየ እኮ!....›› ‹‹ሾርባው ይቅደም!›› ወዘተ የሚሉ የደንበኞች አቤቱታ በጭብጨባ ታጅበው ከዚህም ከዚያም ይሰማሉ፡፡ ጫጫታውና ግርግሩ በአንድ የሐ