ሹመት ብቻ ሳይሆን ሽረትም እንጠብቃለን
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሹመት ፓርላማው አፅድቆታል፡፡ ተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ተሹመዋል፡፡ እያንዳንዱ ሹመት በፓርቲ ውስጥ ተሳትፎን ያረጋገጠ፣ አመኔታ ያሳደረ፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብርን ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ መሆኑን አደራ በማለት ልዩ ትኩረት ሰጥታችሁ አረጋግጡ፣ ወስኑ፣ ፈጽሙ፣ ከማለት በስተቀር ለምን ሾማችሁ አንልም፡፡ ተሿሚዎች ኃላፊነታቸውን በሚፈለገው ብቃት፣ ሥነ ምግባርና ፍጥነት ሲወጡ ለማየት እንጓጓለን እንጂ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ በአጠቃላይ ለመንግሥት፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ለያዘው ኢሕአዴግ አንድ ዓብይና ጠቃሚ እንዲሁም አስቸኳይ የሆነ የምናቀርበው ጥያቄ ግን አለን፡፡ ጥያቄያችንም ስለመሾም ስታስቡ ስለሚሻሩም ታስባላችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ ከተፈለገም ክፍት ቦታ ላይ መሾም ብቻ አይደለም ቁም ነገሩ፡፡ የተያዘ የሥልጣን ወንበር ካለና ወንበሩ ላይ የተቀመጠው ሹምም ብቁ ካልሆነ፣ ከሥልጣኑ በማንሳት የተሻለ መሾም አስፈላጊ መሆኑን አምናችሁ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ናችሁ ወይ? የሚል ነው፡፡ መሾም አለባቸው ከሚለው ጎን ለጎን መሻር አለባቸው የሚባሉ እንዳሉም መታመን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የኃላፊነትና የሥልጣን ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ሥራቸውን በሕግ፣ በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ መወጣት ያልቻሉ አሉ፡፡ በአቅም ማነስ፣ በሥነ ምግባር ጉድለትና በፖለቲካዊ አመለካከት ምክንያት፡፡ መንግሥትም ሆነ ኢሕአዴግ ይህንን ሁኔታ በድፍረትና በቆራጥነት አይተው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃት የማይወጡትን ከኃላፊነት ማንሳት አለባቸው እንላለን፡፡ ብቁዎችን ሾሜያለሁ ከማለት ጎን ለጎን ብቃት የሌላቸውን ሽሬያለሁ ወይም እ