ከመፈክር ይልቅ ዲሞክራሲ!
ሰላም! ሰላም! ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ላላችሁ በሙሉ። አንድ ወዳጄ ይኼንን የአቅጣጫ ሰላምታ እንደማይወደው አጫውቻችሁ አውቃለሁ? ለምንድን ነው ስለው ‹‹የሰው ልጅ እንደ ንፋስ በአቅጣጫ ላይ ተመሥርቶ ሰላምታ ሲለዋወጥ እበሽቃለሁ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? የዘንድሮን ሰው የሚያበሽቀውን ነገር ብዛት ቆጥረን መጨረስ አቃተን! ግን ግን ንፋስን ለምንከተል የዘመኑ ሰዎች ይህ ሰላምታ ካልተሰጠ ለማን ይሰጥ? ለራስ ብቻ የሚሮጥበት ዘመን መሆኑን ካየን ዘንዳ ከዚህ ሌላ ምን ይባላል? አንዳችን ያለ ሌላችን መኖር እንደማንችል እያወቅነው ‘እኔ’ን ብቻ ላማከለ ነፍስ መሮጣችን ይገርመኛል። የሚገርማችሁ ደግሞ አባባልን እንኳ መርጠን አለመጠቀማችን ነው። ለምሳሌ ‹‹ዘመኑ የውድድር ነው›› የሚለውን አባባል ለተቀደሰ ይሁን ለረከሰ ተግባር እንደምንጠቀምበት ሳንለይ ለሁለቱም እንዳሻን እንገለገልበታለን። አሁንማ ሙሰኛውም በሰሞነኛ ተቆጣጣሪዎች ሲያላግጥ ‘ዘመኑ የውድድር ነው’ ማለት ጀምሯል አሉ። ‹‹ውድድሩ ጤናማ ዕድገት ለማስመዝገብ ነው? ወይስ እንደተለመደው ጠልፎ ለመጣል ነው?›› ይሉኝ ነበር ባሻዬ ይኼን ጉድ ቢሰሙ፡፡ ሌባ ቀጪ አጥቶ ለሕዝብ አገልግሎት በሚውል ገንዘብ ደልቦ ሲንጎማለል ይውላል። ተጠቂው ሰፊው ሕዝብ አቧራ ለብሶ ለዕለት ጉርሱ ይማስናል። ፍትሕ የናፈቃት ዓለም። በየጥጋጥጉ ዲስኩር ብቻ ተለጥፎ ይነበባል! ይነበነባል! የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አሁንማ የሰለቸኝ መፈክር ማንበብ ነው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› ብለው፣ ‹‹በመፈክር ውስጥ የተሸጎጡ በርካታ ውሸቶች አሉ፤›› ሲለኝ የገዛ ሳቄ ጆሮዬን አደነቆረው፡፡ ባለፈው ሰሞን አንድ የመንደራችን ጎበዝ ተማሪ ‹‹እኔ ከእንግዲህ ወዲያ ትምህርት የሚባል በቃኝ አቅለሸለሸኝ፤›› ብሎ አቆመው