ድብልቅልቅ ስሜቶችን የፈጠረው የኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት
በዮሐንስ አንበርብር ሰሞኑን ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 18 አገሮችን በሥሩ ለሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል አድርጐ መርጧል፡፡ ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስደንቋል፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን አባል መሆን በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያላገናዘበ ሲሉ ተችተውታል፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አጋጣሚውን የወደዱት ቢመስልም የሰብዓዊ መብት ወቀሳቸው ግን ቀጥሏል፡፡ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ምርጫ 47 መቀመጫዎች ላሉት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ 18 አባል አገሮችን በተተኪ አባልነት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲያገለግሉ መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የ193 አባል አገሮችን ድምፅ የያዘ ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ውስጥ አባል ለመሆን ከ96 በላይ የሚሆኑ አባል አገሮችን ይሁንታ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር ሌሎች ስድስት የአፍሪካ አገሮችም ተመርጠዋል፡፡ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች ያገኙት ድምፅ የተሻለ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ከ193 የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ድምፅ የ178 አገሮችን ይሁንታ በማግኘት ምክር ቤቱን በአባልነት ተቀላቅላለች፡፡ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የፀና እምነት መኖርና ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ፣ የተሻለ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ለዚህ የሚሠሩ ጠንካራ ተቋማት መኖር የምክር ቤቱ አባል ሆኖ ለመመረጥ ከሚያበቁ ዋነኛ መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ምክር ቤቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር በመላው የዓለም አገሮች ውስጥ የሚሠራ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓ