ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ከተሞች የህዳሴ ጉዞ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝ ገለፁ
“ከተሞች የኢንዱስትሪያሊስቶች መፍለቂያ ማዕከል በመሆን የመለስን ራዕይ ያሳካሉ” በሚል መርህ በአዳማ ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት ተጠናቋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በዓሉ በከተሞች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል እና ጠንካሮችን በማበረታታት በዘርፉ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ንቅናቄ መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ የከተሞች የህዳሴ ጉዞ በትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ደመቀ በማደግ ላዩ ያሉ ከተሞችን ወደ ላቀ የልማት ደረጃ ለማሸጋገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በገጠር እየተመዘገበ ያለው የልማት ውጤት በከተሞች እየታየ ላለው መጠነ ሰፊ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡ ከተሞችንና ገጠሮችን አስተሳስሮ መሄድ ቀጣይ የመንግስት አቅጣጫ መሆኑንም ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት፡፡ በ4ኛው የከተሞች ሳምንት ለሰባት ቀናት በቆየው ኤግዚቢሽን ላይ በተለያዩ የከተማ ልማት መስኮች ያከናወኗቸውን ተግባራት እና እራሳቸውን በማስተዋወቅ ከየምድባቸው ላቅ ያለ አፈፃፃም ያስመዘገቡ ከተሞች ተሸልመዋል፡፡ በተለይም በስድስት ቁልፍ የከተማ ልማት ስራዎች የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በ4ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሳምንት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስራዎች የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የትግራይ ክልል ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ስራዎች ደግሞ የትግራይ ክልል አንደኛ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛ እና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል፡፡