Posts

በሲዳማ ዞን ከ12 ሚልዮን ብር የሚበልጥ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ስራ ጀመሩ

Image
አዋሳ ጥቅምት 22/2005 በሲዳማ ዞን ባለፉት ሶስት ወራት ከ12 ሚልዮን ብር የሚበልጥ የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መሰማራታቸውን የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ገለጸ፡፡ በመምሪያው የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በመጀመሪያ ሩብ ዓመት አራት ባለሃብቶች ፈቃድ በማውጣት ስራ ጀምረዋል፡፡ ባለሃብቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ ግብርናና ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙበት አስታውቀው ባለሃብቶቹ በጀመሩት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለ88 ቋሚና 894 ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል። አንዳንድ ከተሞች ላይ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከአምስት ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል፡፡ መምሪያው ለ12 ባለሃብቶች የፈቃድ እድሳትና ተጨማሪ የማስፋፊያ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመው ከዚህ ቀደም ቦታ ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ ባለሃብቶችን በመከታተልና ድጋፍ በመስጠት በፍጥነት ወደ ስራ የሚገቡበትን ሂደት ለማመቻቸት ባደረገው ጥረት 32 ፕሮጀክቶች የአገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡ በሲዳማ ዞን ባለፈው በጀት ዓመት ከ267 ሚልዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 56 ባለሃብቶች በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ በተለይ በይርጋዓለም፣ በወንዶ ገነት፣ በሸበዲኖ፣ በለኩና በበንሳ ከተሞች የሚታየው የባለሃብቶች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲስ ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ከገቡት ባለሃብቶች መካከል አቶ ብርሃኑ አድማሱና ወይዘሪት ሶፋኒት አምዴ ልማታዊ መንግስት ለግል ኢንቨስትመንት እያደረገ ያለው ድጋፍ በርካታ

ሃዋሳን ጨምሮ በደቡብ ክልል በከተሞች ለነዋሪዎች ስኳር ስንዴና የምግብ ዘይት ተከፋፈለ

Image
አዋሳ ጥቅምት 22/2005 በደቡብ ክልል ከተሞች ገበያን ለማረጋጋት ባለፉት ሶስት ወራት 27ሺህ 475 ኩንታል ስኳርና ስንዴ እንዲሁም ከ613ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለተጠቃሚው መከፋፈሉን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ ገለፀ፡፡ የቢሮው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መላኩ እንዳለ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የፍጆታ ሸቀጦቹ የተከፋፈሉት ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ከተሞች በሚገኙ 133 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ነው፡፡ ከተከፋፈለው መካከል 19ሺህ 345 ኩንታል ስኳር፣ 8ሺህ 130 ኩንታል ስንዴና ከ613ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለአባላትና ለአካባቢው ህብረተሰብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ባለፉው የበጀት ዓመትም በ123 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ከ2 ነጥብ 5 ሚልዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ533ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ፣ የምግብ እህልና የተለያዩ ሸቀጦች በተመሳሳይ ለተጠቃሚዎች መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡ http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=3108

በሀዋሳ ከተማ ከ113 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ግብር ተሰበሰበ

Image
አዋሳ ጥቅምት 24/2005 በሀዋሳ ከተማ ባለፉት ሶስት ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከ113 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ ገቢ በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ማከናወኑን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ፡፡ ከከተማው የሚሰበሰበው ገቢ አጠቃላይ ወጪን በሚሸፈንበት ደረጃ ላይ መድረሱም ተመልከቷል፡፡ የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ፍሰሃ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የተሰበሰበው ገቢ ቀጥታና ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከማዘጋጃ ቤትና ሌሎች የግብር ዘርፎች ነው፡፡ ገቢው ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በ13 ነጥብ 5 ሚልዮን ብርና ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜም እጥፍ ያህል ብልጫ እንዳለው ገልጸው ከተሰበሰበው ገቢ የተጨማሪ እሴት ታክስ 54 ነጥብ 5 ሚልዮን ብር እንደሚገኝበት አስታውቀዋል፡፡ ብልጫ ያለው ገቢ የተሰበሰበው ከዚህ በፊት በአስፈፃሚ ሰራተኞችና አመራሩ ላይ የሚታየው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በዲሲፕሊን እርምጃ ስርዓት እንዲይዝና ለግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ሁሉም ግዴታውን እንዲወጣ ጠንካራ የአሰራር አደረጃጀት በመዘርጋቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በከተማው በተለያየደረጃ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ቁጥር ከ10ሺህ 800 በላይ መድረሱን ጠቁመው በግብር ከፋዩ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በአግባቡ የሚስተናገዱበት ግልፅ አሰራር መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ሰፊ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚካሄድበትና ከዚህ የሚመነጨው የገቢ አቅም ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ አሰራር አሟጦ ለመጠቀም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ገቢው በየዓመቱ ጨምሮ ባለፈው ዓመት ብቻ 250 ሚልዮን ብር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ መደበኛና ካፒታልን ጨምሮ 220 ሚልዮን ብር ወጪ በመሸፈን የተረፈው ለመንግስት ፈሰስ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በደቡብ ክልል ከ320 ሚልዮን ብር በሚበልጥ በጀት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ስራ ይካሄዳል ተባለ

Image
አዋሳ ጥቅምት 24/2005 በደቡብ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ320 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 123 ኪሎ ሜትር የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ እንደሚካሄድ የክልሉ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡ ግንባታው ከ36ሺህ ለሚበልጡ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠር ተጠቁሟል፡፡ የቢሮው የመሰረተ ልማት አቅርቦትና አስተዳደር ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አምሩላህ ጠለሀ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ስራው የሚከናወነው በክልሉ 14 ዞኖችና 4 ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ 22 ከተሞች ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ በሚገነባው የድንጋይ ንጣፍ መንገድ በሚፈጠረው የስራ ዕድል ከ36ሺህ በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመጠቆም ከእነዚህም መካከል ወደ 13ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ በከተሞች የሚሰራው መንገድ በአማካይ 8 ሜትር ስፋትና 123 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው እንደሚሆን ገልጸው የዚሁ ግንባታ ወጪ 140 ሚልዮን ብር በክልሉ መንግስት ቀሪው በከተሞች ማዘጋጃ ቤቶች፣ከአለም ባንክና ከጀርመን መንግስት ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡ የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ከአስፓልት የማይተናነስና በዝቅተኛ ወጪ ለረጅም ዓመታት ያለብልሽት የሚያገለግል ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነባር መንገዶች፣ ጥርጊያና ጥገና፣ የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ግንባታና ማሻሻያ፣ የቱቦ ቀበራ፣ የእግረኛ መተላለፊያ ፣ የመንገድ መብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታን ጨምሮ ከ2ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ በደቡብ ክልል ባለፈው በጀት ከ146 ሚልዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ከ59 ኪሎ ሜትር በላይ የድንጋይ ንጣፍ መገንባቱንና ከ26ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶ

ሀዋሳ መንገድ ላይ ትልቅ ኣየር ማረፊያ ልገነባ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ለሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ድጋፋቸውን ሰጡ -     የቦሌ መንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ ሥራ ሊካሄድ ነው በቃለየሱስ በቀለ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት በሞጆ አካባቢ ለመገንባት ላቀደው ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ድጋፋቸውን ገለጹ፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅት አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንተርፕራይዙን በኤርፖርት ግንባታው ዕቅድ ላይ ቀጣይ ሥራ እንዲሠራ መመርያ ሰጥተውታል፡፡ አዲስ ስለሚገነባው ኤርፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በቅርቡ የሰጡት የትራንስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ የአዲሱ ኤርፖርት ግንባታ ፕሮጀክት ዕቅድ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የሚፀድቅ ሲሆን፣ በመቀጠል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚሆን ገንዘብ ከቻይናው ኤግዚም ባንክ እንደሚጠየቅ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባት ያስፈለገበት ምክንያት የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጨናነቀ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍጥነት በማደጉና በርካታ አውሮፕላኖች በመግዛት ላይ በመሆኑ፣ የተለያዩ አገሮች አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ በረራ መጀመራቸው ለኤርፖርቱ መጨናነቅ እንደ ምክንያት ተቆጥሯል፡፡ በተጨማሪም መደበኛ የበረራ አገልግሎት፣ ጄነራል አቪዬሽን (መደበኛ ያልሆነ የቻርተር በረራ አገልግሎት) እንዲሁም የ‹‹ቪአይፒ›› በረራዎች በአጠቃላይ በአንድ ኤርፖርት መስተናገዳቸው የሥራ ጫና ፈጥሯል፡፡ በተለይ እንደ ሴስና ያሉ ትናንሽ አውሮፕላኖችንና እንደ ቦይንግና ኤርባስ ዓይነት ትላልቅ አውሮፕላኖችን በአንድ ኤርፖርት